ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እና የግሪክ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል- አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 17/2017 (ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ እና በግሪክ መካከል ያለው የመንግስታት እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

በግሪክ ፓርላማ አባልና የኦርቶዶክስ ኢንተርፓርሊያመንት ጉባኤ (IAO) ኃላፊ ማክስሞስ ቻራኮፖሎስ (ዶ/ር) የተመራው የልኡካን ቡድን ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ጉብኝት አድርጓል።

የልዑካን ቡድኑ አቶ ታገሰ ጫፎ እና በምክር ቤቱ የኢትዮጵያ እና የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት የወዳጅነት ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይቷል።

አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የሁለቱ አገራት ለረጅም ጊዜ የቆየ የመንግስታት እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከግሪክ ጋር ንግድና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ልምድ መቅሰም እንደምትፈልግና ያላትን መልካም ተሞክሮም ለማካፈል ዝግጁ ናት ብለዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ እና የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት የወዳጅነት ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ እና ግሪክ ለረጅም አመታት ያላቸውን ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሁለቱ ሀገራት በቴክኖሎጂ፣ በንግድ፣ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በኢነርጂ እና በተለያዩ ዘርፎች ተባብረው ቢሰሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ አንስተዋል።

የሁለቱ ሀገራት ምክር ቤቶች ተቀራርበው በመስራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

በግሪክ ፓርላማ አባልና የኦርቶዶክስ ኢንተርፓርሊያመንት ጉባኤ (IAO) ኃላፊ ማክስሞስ ቻራኮፖሎስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ግሪክ በቱሪዝም እና በግብርናው ዘርፍ ከኢትዮጵያ በርካታ ልምዶችን መቅሰም እንደምትፈልግ እና በዘርፉ አብሮ ለመስራት ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

ግሪክ በኮንስትራክሽን፣ በባህር ትራንስፖርት እና በተለያዩ የቴክኖሎጂ ዘርፎች ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል እንደምትሻም አመልክተዋል።

የግሪክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን የኢንስትመንት ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባ ኃላፊው መናገራቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም