በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን በመምህራን ላይ የሚያደርሰው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በጽኑ የሚወገዝ ነው - የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን በመምህራን ላይ የሚያደርሰው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በጽኑ የሚወገዝ ነው - የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 17/2017 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን በየጊዜው በመምህራን ላይ የሚያደርሰው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በጽኑ የሚወገዝ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) ገለጹ።
በክልሉ ተማሪዎች የመማር መብታቸው እንዲከበር ወላጆች እና የትምህርት ማህበረሰቡ ድርጊቱን ማውገዝና መታገል እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፥ ማህበሩ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ያሉትን አባላቱን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ እየተጋ ይገኛል፡፡
በተጨማሪ የመምህራን መብታቸውና የሙያ ክብራቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ይህም ቢሆን ግን የመምህራንን ሙያዊ ክብር ዝቅ የሚያደርግ ኢ-ሰብዓዊ ተግባር ሲፈጸም እንደሚስተዋል ጠቁመው፤ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን በመምህራን ላይ የሚፈጽማቸውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ለአብነት አንስተዋል፡፡
ይህም ማህበሩ ድርጊቱን አጥብቆ እንደሚያወግዘው ገልጸው፤ ድርጊቱ ትምህርት ቤቶች ደህንነታቸው የተረጋገጠ መሆን አለበት የሚለውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መርህ በእጅጉ የጣሰ ነው ብለዋል።
በክልሉ አንዳንድ ቦታዎች የተቋረጠውን የመማር ማስተማር እንቅስቃሴ ወደ መደበኛ ስራ እንዲመለስ ከሚመለከታቸው ጋር በህብረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
መምህርራን የማስተማሪያ ቁሳቁስ ባልተሟላበት ሁኔታ የሚሰሩ መሆናቸውን ያመለከቱት ማህበር ፕሬዚዳንት ዮሐንስ (ዶ/ር)፤ ይህን ተቋቁመው ሙያዊ ሀላፊነታቸውን ለመወጣት በሚያደርጉት ጥረት ኢ ሰብዓዊ ድርጊት ማድረስ ሀላፊነት የጎደለው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ ትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚደርሰውን ተጽዕኖ በቅርብ እየተከታተልን ነው ያሉት ማህበር ፕሬዚዳንት ዮሐንስ (ዶ/ር)፤ በማንኛውም ወቅት መምህራን ላይ የሚደርስ ጥቃትን አጥብቀን እንቃወማለን ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ አጠቃላይ በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ከ40 በመቶ እንደማይበልጥ የገለጹት ዮሐንስ (ዶ/ር)፤ ጽንፈኛው የመማር ማስተማር ሂደት ማስተጓጎሉ የማህበረሰቡንም የክልሉንም የትምህርት ሁኔታ ወደ ኋላ የሚጎትት መሆኑን ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ክፍት መሆን አለባቸው ያሉት የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ (ዶ/ር)፤ ሁሉም ማህበረሰብ በተለይ ወላጆች የቅድሚያ ተጎጂ በመሆናቸው ጽንፈኛውን በቃህ ሊሉት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቶች ያሉት በየቀበሌው በመሆኑ ወላጆችና የትምህርት ማህበረሰቡ ተማሪዎች የመማር መብታቸው እንዲከበር እና የመማር ማስተማሩ በተሟላ መልኩ እንዲካሄድ መምከር መገሰጽ እንዲሁም መታገል እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አፍሪካን በመወከል የዓለም የመምህራን ማህበር ስራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል ነው።