ቀጥታ፡

የኤሌክትሪክ መሠረት ልማት ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል -የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 17/2017 (ኢዜአ)፦የኤሌክትሪክ መሠረት ልማት ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ።

አገልግሎቱ ከሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ግብዓት አምራቾች ጋር የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።

የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ግብዓት ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ምርት ሙሉ በሙሉ መሸፈን ወደ ሚያስችል የማምረት ደረጃ መሸጋገር እንደሚገባም በዚሁ ወቅት ተጠቁሟል፡፡

የአገልግሎቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦትን ተደራሽና አስተማማኝ ለማድረግ በርካታ የሪፎርም ስራዎች ተሰርተዋል።

የምክክር መድረኩ ዋና አላማ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ግብዓትን በተሻለ አቅም በሀገር ውስጥ በማምረት ፍላጎትን ሙሉ ለሙሉ መሸፈን እንዲቻል የጋራ መግባባት ለመፍጠር ነው ብለዋል።

በጅምር ደረጃ በሀገር ውስጥ እየተመረተ ያለውን ግብዓት በቀጣይ በሙሉ አቅም በማምረት የቴክኖሎጂ ሽግግር ማረጋገጥና የውጭ ምንዛሪን ማዳን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይገባ የነበረውን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ግብዓት በሀገር ውስጥ መተካት የሚያስችል ስራ እየሰሩ ለሚገኙ አምራቾችም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም