ቀጥታ፡

የህልውና ጉዳይ በሆነው የባህር በር ጥያቄ ላይ የመንግስትን የዲፕሎማሲ ጥረት እንደግፋለን - የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

ሰመራ፤ ሚያዝያ 17/2017(ኢዜአ)፦ መንግስት የህልውና ጉዳይ በሆነው የባህር በር ጥያቄ ላይ አቋም በመያዝ የጀመረውን የዲፕሎማሲ ጥረት የሚደግፉት መሆኑን የተለያዩ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።

በምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ እያንቀሳቀሰች የምትገኘው ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ የባህር በሯን በማጣቷ ለከፍተኛ ወጭ በመዳረግ ዋጋ እየከፈለች መሆኑ ይታወቃል።

ከ120 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት የብዙ ህዝብና የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ሀገር ያለ ባህር በር ተዘግታ መኖር የለባትም በሚል መንግስት ፅኑ አቋም ይዞ እየሰራ ይገኛል።


 

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የህልውና ጉዳይ መሆኑን አቋም በመያዝ መንግስት የጀመረው የዲፕሎማሲ ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

በአፋር ክልል ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር ፓርቲ (አነግፓ) ሊቀ መንበር ሐንፈሬ አሊሚራህ፤ ኢትዮጵያዊያን ቀይ ባህርን በቅርበት እየተመለከቱ የባህር በር ተጠቃሚ አለመሆናቸው በየትኛውም መመዘኛ ትክክል አይደለም ብለዋል።

በመሆኑም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በመንግስት እየተደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው በተለይም የባህር በር ጥያቄው የሁላችንም ጉዳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ አነግፓ የመንግስትን የዲፕሎማሲ ጥረት በማገዝ ከፊት የሚሰለፍ መሆኑን አረጋግጠው የሀገርን ብሄራዊ ጥቅም ማስቀደም የሁላችንም አጀንዳ መሆን አለበት ብለዋል።

የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር(አርዱፍ) ምክትል ሊቀ መንበር አቶ መሐመድ አወል ወግሪስ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑ እርግጥ ነው ሲሉ ተናግረዋል።


 

በመሆኑም መንግስት የጀመረውን የዲፕሎማሲ ጥረት በማገዝ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት እንድትሆን በሚቻለው ሁሉ እግዛ እናደርጋለን ብለዋል።

የአርጎባ ብሄረሰብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (አብዴን)ፀሐፊ አቶ በክሪ አህመድ፤ የባህር በር ጥያቄው ለኢትዮጵያዊያን የህልውና ጉዳይ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም የመንግስትን የዲፕሎማሲ ጥረት በማገዝ ያለምንም ልዩነት ለሀገር ህልውናና ብሄራዊ ጥቅም በጋራ እንሰራለን ብለዋል።

የመንግስትን የዲፕሎማሲ ጥረት ፓርቲያቸው መሉ በመሉ የሚደግፈውና ለተፈፃሚነቱ የሚያግዝ መሆኑንም አረጋግጠዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም