ሰብዓዊ ድጋፍን በዘላቂነት በራስ አቅም ለመሸፈን በክልሎች ስኬታማ ስራ እየተሰራ ነው-አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ሰብዓዊ ድጋፍን በዘላቂነት በራስ አቅም ለመሸፈን በክልሎች ስኬታማ ስራ እየተሰራ ነው-አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 17/2017 (ኢዜአ)፦ሰብዓዊ ድጋፍን በዘላቂነት በራስ አቅም ለመሸፈን በሁሉም ክልሎች ስኬታማ ስራ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) ገለጹ።
ኮሚሽነሩ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፎችን በራስ አቅም በማሟላት ከተረጂነት ለመላቀቅ እያከናወነች ያለችውን ተግባር አስመልክተው ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን በራስ ሃብት መቋቋም የሚያስችል አቅም እየፈጠሩ እንደሚገኙም አንስተዋል፡፡
መንግሥት የኢትዮጵያን የተረጂነት ታሪክ ለመቀየር ልዩ ትኩረት መስጠቱን ጠቁመው፥ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የተሳተፉበት ውይይት በማድረግ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን እንደሚቻል መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሰፊ የሚታረስ መሬት፣የውሃ ሃብት እና በርካታ የተማረ ሰው ሃይል ያላት ሀገር መሆኗም የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም መሆኑን አንስተዋል፡፡
የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ብሔራዊ ደህንነትን የማስጠበቅ ጉዳይ እንደሆነ በመጥቀስ፥ የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም በመሸፈን የሀገር ክብርን ለማስጠበቅ እየተጋን ነው ብለዋል።
መግባባት፣መዘጋጀት እና በተቀናጀ መንገድ የልማት ስራን ማፋጠን ተረጂነትን ለማስወገድ ወሳኝ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
በዚህ መርህ መሰረት ብሔራዊ የመጠባበቂያና የዕለት ደራሽ የምግብ ክምችትን ለማሟላትም በሁሉም ክልሎች ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።
የእስካሁኑ እንቅስቃሴም ትልቅ ስኬት እየተመዘገበበት ነው ብለዋል።
ተረጂነትን ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት እንደሚቻል በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በሌማት ትሩፋትና በኢንዱስትሪ ዘርፎች እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀው የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ ለሰውሰራሽና ለተፈጥሯዊ አደጋዎች በራስ አቅም ምላሽ የመስጠት አቅምን እንደሚያጎለብትም አንስተዋል።
ይህም የውጭ እርዳታ ጥገኝነትን በማስቀረት ሰብዓዊ ድጋፍን በዘላቂነት በራስ አቅም ለመሸፈን እና የተሟላ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ገልጸዋል።