ቀጥታ፡

ለስደትና ፍልሰት ዘላቂ መፍትሄ ለመፍጠር ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር ይገባል- ምሁራን

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 16/2017(ኢዜአ)፦ለስደትና ፍልሰት ዘላቂ መፍትሄ ለመፍጠር ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስደትና ፍልሰት ጥናት ማዕከል ከዓለም አቀፉ ቀጣናዊ ዘላቂ መፍትሄ ሴክሬታሪያት ተቋም ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ ጉባኤ በአዲስ አበባ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

በጉባኤው ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝደንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)፣ የዩኒቨርሲቲው የስራ ኃላፊዎች፣ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን፣ በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ጆሹዋ ታባህን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

ከካናዳ፣ ከምስራቅ አፍሪካ እና ከ19 የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የተጋበዙ የዘርፉ ምሁራን፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የልማት አጋሮች፣ ፖሊሲ አውጭዎችና አስፈጻሚዎችም በጉባኤው ላይ ታድመዋል።

ጉባኤው “በግዳጅ ስደትና ፍልሰት ላይ የደቡባዊው ዓለም ዕይታ በፖሊሲ፣ ምርምርና ትግበራ ጥምርታ አንጻር ሲቃኝ” በሚል መሪ ሀሳብ የሚደረግ ነው።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በቀጣናው ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸው መፈናቃላቸውን ገልጸዋል።

ይህን መሰል መድረክ መዘጋጀቱ መፍትሄዎች ላይ ለመወያየት ዕድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።

የስደትና የፍልሰት ችግሮችን ለመፍታት ዘርፈ ብዙ ስራዎች እንደሚጠበቁ የገለፁት የጉባኤው ተሳታፊዎች ለስደትና ፍልሰት ዘላቂ መፍትሄን ለመፍጠር ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።

በሰዎች መፈናቀል እና ስደት ላይ ያተኮሩ ምርምሮች፣ ፖሊሲዎች እና ተፈጻሚ የሚሆኑ ስልቶች ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸው የዩኒቨርሲቲው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም