ቀጥታ፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) መልዕክት፡-

የከተማዋን ገጽታ በእጅጉ የቀየረ ስራ! አለማድነቅ ንፉግነት ነው!

የካዛንቺስ የኮሪደር ልማት እስካሁን በከተማዋ ከተገነቡት የኮሪደር ልማት ስራዎች በውስጡ ባስተሳሰራቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች የተለየ ገፅታን የፈጠረ ነው፤ የቀደመውን የአካባቢዉን ምስቅልቅል ሁኔታ በአይነ ህሊናው ለሚያይ፣ በተለይ በዕለት ተዕለት ህይወቱ አከባቢውን ሲያስተውል ለነበረ የከተማው ነዋሪ በኮሪደር ልማቱ የተፈጠረው አዲስና ውብ ገፅታ በምናብ ከሚያውቀው የውብ እይታና ሀሴት ነፀብራቅ ተምሳሌት ከሆነው የገነት ፀዳል አንዳች ሀሳብ ተውሶ ከተማችንን ወደ ምድራዊ ገነት እየቀየርናት ይሆን? ብሎ እንዲጠይቅ ያነሳሳል። ይህን የከተማዋን ገጽታ በእጅጉ የቀየረ የካዛንችስን ድንቅ ስራ አለማድነቅ ንፉግነት ነው!!

ከሰሞኑም የከተማችን ሰው ተኮርና ሁለንተናዊ አገራዊ ለውጥ አካል የሆነው የካዛንቺስ ኮሪደር ልማት፣ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ ተመርቆ ለህዝብ አገልግሎት ክፍት ሆኗል። የካዛንቺስ የኮሪደር ልማት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሁለተኛ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት አካል ነው።

የኮሪደር ልማቱ ካዛንቺስን ውብ በማድረግ አካባቢውን ካላበሰው አዲስ ገጽታ ባሻገር በዘመናዊነቱም ይጠቀሳል።

ለአዕምሮ ሀሴትን የሚፈጥሩና ለእይታ የሚማርኩ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠርና ጽዱ አካባቢን ለነዋሪው በመለገስ ሌላ አዲስ ተጫማሪ የመዝናኛ ስፍራን ለከተማዋ፣ በተለይም ለነዋሪዎቿ አበርክቷል፡፡ የከተማዋንም ገጽታ አንድ ደረጃ ክፍ ያደረገው ይህ ግንባታ የኢትዮጵያ ብልጽግና እና ትንሣኤ አይቀሬ መሆኑንም ያመላክተ ነው፡፡ ሁሉን ያቀናጀ የከተማ ግንባታ (smart city) አካል በመሆኑ ለዘመናዊ ከተማ ግንባታችን ሞዴል ተደርጎ የሚወሰድም ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየተገነቡ ያሉ ኮሪደሮች ትስስር እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር የከተማዋ ገጽታ በመሰረታዊነት እየተቀየረ መሆኑን አይተናል፡፡ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብና “አዲስ አበባ” እያደረጓት ነው፡፡

ዘመናዊ የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች መስፋፋታቸው እና የተሳለጡ መሆናቸው ለኮሪደር ልማት ስራዎች እንደ ጀርባ አጥንት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ግንባታዎች የሰውና የተሽከርካሪ መጓጓዣ መንገዶችን፣ የፍሳሽ ማስወገጃ፤ የመብራት፣ የስልክ እና ኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታዎች፣ የመዝናኛና የማረፊያ ቦታዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሰፍራዎች ወዘተ የሚያካትቱ ናቸው፡፡


 

መሰረተ ልማቶቹ በከተሞች የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማስተሳሰር በሁሉም አቅጣጫ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ናቸው፡፡ በመሠረተ ልማቶቹ ዝርጋታም ሆነ በመልሶ መልማት ከቦታው የሚነሱ ነዋሪዎች የሚዛወሩባቸውን የመኖሪያ መንደሮች ጭምር የሚያካትቱ ናቸው፡፡ መኖሪያ መንደሮቹ ዘመናዊ ከመሆናቸው ባሻገር ለነዋሪዎች እንዲመቹ እንደ ትምህርት ቤት፣ ወፍጮ ቤቶች፣ የዳቦና እንጀራ መጋገሪያ እንዲሁም የአቅመ ደካሞች መመገበያ ማዕከሎችን ያካተቱ ናቸው፡፡ ልማቱ ሁሉን አቀፍ፣ አካታች እና ሰው ተኮር ነው የሚባለውም ለዚሁ ነው።

የመዝናኛ ስፍራዎቹ ከማዝናናት ባሸገር አዕምሮን ለማሳረፍ፣ ከራስ ጋር ለመታረቅ፣ በንባብ አዕምሮን ለመገንባት፣ በስፖርት አካልን ለማበልፀግ ታሳቢ ተደርገው የተገነቡ ናቸው። የአረንጓዴ ስፍራዎች ከአካባቢያቸው ጋር የተስማሙ ዘላቂ የከተማ ልማት (Sustainable and environmentally friendly cities) የመገንባት አቅጣጫን የተከተሉ ናቸው።

ይህን ዘመናዊ፣ ሁሉን አካታች፣ ቅርስን በማቆየት ለዛሬው የተመቸ፣ ለነገው ትውልድ ተሻጋሪ የሆነንን አኩሪ ስራ አንዳንድ ሰዎች ባለማወቅም ይሁን ሆን ብለው "ብልጭልጭ ነገር" ብለው ሊያሳንሱት ሲሞክሩ ይታያል። አንዳንዶቹ ደግሞ ሰብዓዊነት ለምን አይቀድምም ሲሉ ይደመጣል። መነሻቸው ምንም ይሁን ምን ትችቶቹ ከሰው ተኮር ልማቱና አገርን በማበልፀግ ህዝብ የተሻለ ህይወት እንዲኖር ለማድረግ ከተያዘው መሠረታዊ መርሆዎች ያፈነገጡ ናቸው።

ምክንያቱም የአንድ ከተማ ዕድገት ቁልፍ መለኪያ የሚባሉት ከላይ በዝርዝር የቀረቡ መሠረተ ልማቶች ምን ያህል አካታች በሆነ መንገድ ተሟልተዋል? ለነዋሪዎች ምቹ የሆነ አግልግሎት ቀርቧል ወይ? የሚለው ነው።

ትችቱ፣ ከቁልፍ መሠረተ ልማቶቹ አንዱ በሆነው የመንገድ ዳር መብራት ጉዳይ የሚቀርብ ከሆነም እሱም ስህተት ነው። ምክንያቱም በጣም አድጓል ተብለው ለከተሞች ደረጃ ለመፈረጅ ጥቅም ላይ ከሚውሉ መሥፈርቶች አንዱ በሌሊት ከተሞቹ ከሳተላይት በሚወሰዱ መረጃዎች ምን ያህል ብርሃናማ ናቸው የሚል ነው።

ብርሃን በእጅጉ ደምቆ የሚታይበት ከተማ ብቁ መሠረተ ልማት ያሟላና ያደገ ተደርጎ ይወሰዳል። ነዋሪዎቹም ደስተኞች ሆነው የሚኖሩበት፣ ወንጀል በስፋት የማይታይበት እና የብልጽግና ተምሳሌት ተደርገው ይወሰዳሉ። በአንጻሩ በጭለማ የተዋጡ ከተሞች መሠረተ ልማት ያልተገነቡላቸው፣ ወንጀል የሚበዛባቸው፣ ነዋሪዎቹም በምቾትና በደህንነት ከመኖር አንፃር ተስፋ የሚያጡባቸው ናቸው።

መጀመሪያ ሰብአዊነት አይቀድምም ወይ ለሚሉት ደግሞ ምላሹ ከዚህ የተሻለ ምን አይነት ሰብአዊነት አለ የሚል ነው፡፡

እጅግ ለመኖር አስቸጋሪ ከሆነና ከተጎሳቆለ አካባቢ፣ ንጹህ መጠጥ ውሃ እና የመጸዳጃ ስፍራ ከማይገኝበት፣ ሰው እና ተሽከርካሪ እየተጋፉ ከሚጓዙበት ውስብስብና ጭንቅንቅ መንገዶችና አከባቢዎች በመውጣት እነዚህ ጉዳዮች በተሟሉበት ከባቢና አውድ መኖር እንዴት ሰብዓዊነትን ማጣት ይሆናል?

አዛውንቶች መውጫና መግቢያ አጥተው ከሚንከራተቱበት፣ በደሳሳ ጎጆ እንዲታፈኑ ከተገደዱበት፣ ህፃናትና ወጣቶች ለማህበራዊ ጠንቆች ከሚጋለጡባቸው አካባቢዎች ተነጥለው ለመኖር እጅግ ምቹ ወደ ሆኑ የተቀናጀ ማህበራዊ አገልግሎት የሚያገኙባቸው፣ የተሻሻለ የኑሮ ዘይቤ ወደሉባቸው አካባቢዎች መዛወራቸው እንዴት ሰብዓዊነትን መፃረር ተደርጎ ይወሰዳል? ይህ የሰብዓዊነት መለኪያውስ ምን ይሆን ያስብላል። ዜጎችን በተሻለ የህይወት ደረጃና ጤንነት እንዲኖሩ ከማድረግ የበለጠ ምንስ ሰብአዊነት አለ? ብሎ ህሊናን መጠየቅ ግድ ይላል፡፡

ለነገሩ ከተቺዎቹ በላይ ህዝቡ፣ በተለይም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከካዛንቺስ ኮሪደር ልማት አስቀድመው የካዛንቺስ ልማት ተነሺዎች አዲስ ህይወት በጀመሩበት የገላን ጉራ አካባቢ ነዋሪዎቹን ባገኙበት ወቅት ነዋሪዎቹ ያሳዩት የማይረሳ የደስታና ሀሴት ብስራት ገላጭ መልዕክት እውነታውን አሳውቆናል።

በተለይ ምክንያት አልባ በሆነ የሁልጊዜ ጨለማ እይታ የሚተቹ ወገኖች መገንዘብ ያለባቸው ጉዳይ የከተማ ነዋሪዎችም እንደ የትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች ብቁ ማህበረ ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን የማግኘት እና ምቹ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት ያላቸው መሆኑን ነው።ለራስ የፖለቲካ ጥቅም ሲባል ሌላውን ደፍቆና አሳንሶ እንዲኖር ማድረግ ህሊና ቢስነት ነው። ዜጎች በራሳቸው እንጡራ ሃብት እና ከራሳቸው በሚሰበሰብ ግብር አካባቢያቸውን የማልማት መብት እንዳለቸው ልብ ሊባል ይገባል፡፡

በጥቅሉ ከአዲስ አበባ የምንወስደው ተሞክሮ የኮሪደር ልማት ስራ በስፋት የሚታይባቸው አካባቢዎች ዜጎች ተቺዎችን ወዲያ ብለው ከአስተዳደራቸውና ከጸጥታ ኃይል ጋር ተቀናጅተው እንዲሁም እጅ እና ጓንት ሆነው ሰላማቸውን በማስከበር መልማት ይኖርባቸዋል፡፡

መለስተኛ ችግር በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ያሉ ወገኖቻችንም እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞቻችንን ፈልግ የመከተል እና የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት መጠበቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ ይህንን ሲያደርጉም ልማታቸው እየተፈጠነ፣ ተጠቃሚነታቸው እየተረጋገጠ ይሄዳል፡፡ ካዛንቺስን አለማድነቅ ግን ንፉግነት ነው‼️

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም