ቀጥታ፡

በከተማዋ ተሰናስለው የተሰሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው - የኢኮኖሚ ዘርፍ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች

አዲስ አበባ፣ሚያዝያ 16/2017 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ ተሰናስለው የተሰሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን የፌዴራል መንግስት የኢኮኖሚ ዘርፍ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ገለጹ።

የፌዴራል መንግስት የኢኮኖሚ ዘርፍ ተቋማት የስራ ኃላፊዎችና ሙያተኞች የካዛንችስ ኮሪደር ልማትን ጨምሮ የመዲናዋን የኮሪደር፣ የከተማ ግብርና እና መልሶ ግንባታ የልማት ስራዎች ጎብኝተዋል።

በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የሀገራዊ የተቀናጀ መሰረተ ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ቴዎድሮስ ተገኝ እንደገለጹት፥ የመዲናዋ የልማት ስራዎች ከተማን ከማስዋብ የተሻገሩ ሰው ተኮር ስኬታማ ፕሮጀክቶች ናቸው።

በተለይም የካዛንችስ ኮሪደር ልማት ተነሺዎችን ከጎስቋላ ኑሮ በማላቀቅ በዘመናዊ የመኖሪያ መንደር እንዲኖሩ ያስቻለ ውጤታማ የልማት ስራ መሆኑን እንደተገነዘቡ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ በተሰናሰለ አግባብ የተከናወኑ የመሰረተ ልማት የቅንጅት ስራዎችን በሌሎች ከተሞችም በማስፋት በትኩረት እተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በሌላ መልኩም በቅንጅት ክፍተት የሚከሰተውን የሀገር ሃብትና የጊዜ ብክነት በተሰናሰለ የመሰረተ ልማት ግንባታ የነዋሪዎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ሥራ አስፈፃሚ ሰጠኝ አዲሱ እንደገለጹት፤ የመዲናዋ የልማት ስራዎች የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ኢኮኖሚና ጽዱ ከተማ ግንባታ ርዕይ እውን የሚያደርጉ ናቸው።

ለአብነትም የቴሌ፣ የኤሌትሪክ ኃይል፣ ውሃ፣ መንገድና ሌሎች በቅንጅት የሚሰሩ የመሰረተ ልማት ስራዎችን የሃብትና የጊዜ ብክነት በማስተካከል ጥሩ ተሞክሮ የተገኘበት መሆኑን እንደተገነዘቡ ገልጸዋል።

የልማት ስራዎቹ በተሻለ ፍጥነትና ጥራት መጠናቀቃቸውም በዕቅድ የተያዙ ፕሮጀክቶችን በውጤታማነት በመፈጸም ትልቅ ትምህርት የሰጡ እንደሆኑም ተናግረዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የከተማ ግብርና ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ስለሺ በቀለ፤ በመዲናዋ የተሰሩ ውብ የመሰረት ልማት ግንባታዎች በሕይወት ዘመኔ ለሀገሬ ስመኝና ሳልመው የነበረ ነው ያሳየኝ ብለዋል።

የአዲስ አበባ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችም የዜጎችን የዕለት ከእለት ኑሮ ከተፈጥሮ ጋር በማሰናሰል ለነዋሪዎች ዘመናዊና ሰላማዊ የአኗኗር ዘይቤን የፈጠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ የተቀናጀ የእንስሳት ልማት ልህቀት ማዕከልም የገበያ አቅርቦት ፍላጎትን በመሙላት ዜጎችን በተመጣጣኝ ዋጋ በከተማ ግብርና ምርት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን እንደተመለከቱ አስረድተዋል።

በቱሪዝም ሚኒስቴር የሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና መከታተያ ሥራ አስፈፃሚ ጅብሪል ሉጂያ÷ አዲስ አበባን ውብ ገጽታ ለማላበስ በተከናወኑ የልማት ስራዎች ላይ ተሳትፎ ያደረጉ ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

የመዲናዋ የኮሪደር ልማት ስራዎች የልማት ተነሽዎችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ በማድረግ በዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ህይወታቸውን እንዲመሩ ያስቻሉ መሆናቸውን በጉብኝታቸው እንደተመለከቱ ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት በተለያዩ የገበታ ፕሮጀክቶች በመዲናዋ የተከናወኑ የልማት ስራዎችም የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ለሀገር ዕድገት ገንቢ ሚና እንዲወጣ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የመንግስት የኢኮኖሚ ዘርፍ የስራ ኃላፊዎችና ሙያተኞች ጉብኝትም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዕድገት እያስመዘገበች የምትገኘውን ስኬት የተግባር ምልከታ ለማድረግ ያለመ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም