የክፍያ ስርዓቱ ጠንካራ እና ተአማኒነት ያለው የፋይናንስ ስርዓት ለመገንባት ያስችላል- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ - ኢዜአ አማርኛ
የክፍያ ስርዓቱ ጠንካራ እና ተአማኒነት ያለው የፋይናንስ ስርዓት ለመገንባት ያስችላል- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 16/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ከሰው ንክኪ ነጻ የክፍያ ስርዓት (EATS) ጠንካራ እና ተአማኒነት ያለው የፋይናንስ ስርዓት ለመገንባት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።
ብሔራዊ ባንክ ማሻሻያ የተደረገበትን ዘመናዊ የክፍያ ስርዓት ዛሬ ይፋ አድርጓል።
የክፍያ ስርዓቱ የፋይናንስ ተቋማት የኤሌክትሮኒክስ መረጃ የሚለዋወጡበትን ዓለም አቀፍ መመዘኛ “ISO 20022” ያሟላ መሆኑን አመልክቷል።
ስርዓቱ የኢትዮጵያን የክፍያ መሰረተ ልማት በማዘመን፣ ፍጥነት እና ደህንነትን በማሳደግ እንዲሁም በባንኮች መካከል ከፍተኛ መጠን ያለው የገንዘብ ልውውጥ ለማካሄድ እንደሚያስችል ነው የገለጸው።
ከ35 በላይ የፋይናንስ ተቋማት የክፍያ ስርዓቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጸው ባንኩ፥ ይህም ጠንካራ እና ተአማኒነት ያለው የፋይናንስ ስርዓት ለመገንባት እንደሚያስችል አመልክቷል።
ነባሩ የኢትዮጵያ ከሰው ንክኪ ነጻ የክፍያ ስርዓት (EATS) ከእ.አ.አ 2011 አንስቶ ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል።