ምክር ቤቱ የክልሉ ግብርና ሽግግር ሂደት እንዲፋጠን እያገዘ ነው -አቶ ሽመልስ አብዲሳ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ የክልሉ ግብርና ሽግግር ሂደት እንዲፋጠን እያገዘ ነው -አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 16/2017(ኢዜአ)፦የኦሮሚያ ክልል የግብርና ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት የክልሉ የግብርና ሽግግር ሂደት እንዲፋጠን የተሻለ እገዛ እያደረገ መሆኑን የክልሉ ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
በኦሮሚያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት 3ኛ ጉባዔ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት ተካሄዷል።
በጉባዔው ላይ የተገኙት የክልሉ ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ፥ የግብርና ዘርፉ ከፍተኛ ውጤት እየተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል።
በእስካሁኑ ሂደት ከፍተኛ ውጤት እየተገኘበት ያለውን የግብርና ዘርፍ የበለጠ ለማሳደግና ለማስፋፋት ምክር ቤቱ በጎ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
የኦሮሚያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ከተመሰረተ ጀምሮ በጥናት ላይ ተመርኩዞ ባከናወነው ስራ ጥሩ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ የክልሉ መንግስት የሚፈልገውን ያህል ውጤታማ እንዲሆን የጀመረውን ሥራ እንዲያጠናክርም ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል።
ከዚህም ባለፈ ምርትና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ በግብርና ኤክስቴንሽን የተጋዙ አዳዲስ ኢንሼቲቮች በመንደፍ የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ መስራት እንደሚገባም አስረድተዋል።
የአርሶ አደሩን ግንዛቤና ዕውቀት የሚያሳድጉ፣ምርታማነትን የሚጨምሩ፣ የገበያ ትስስር ችግሮችን የሚፈቱ የጥናትና ምርምር ሥራዎችንም በትኩረት እንዲያከናወኑም አሳስበዋል።
የምክር ቤቱ ጥረት እንዲሳካ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና ክላስተሮች የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡም አቶ ሽመልስ አስገንዝበዋል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የኦሮሚያ ክልል በግብርናው ዘርፍ እያስመዘገበ ያለው ሽግግር ለሌሎች ክልሎችም ልምድ የሚሆን ነው ብለዋል።
የምክር ቤቱን ዓላማ የበለጠ ለማሳካት ሁሉም የምክር ቤቱ አባላት ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዲወጡም ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
በክልሉ ግብርናውን ከተለመደው አሰራር በማላቀቅ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ ናቸው።
ይህንኑ ሂደት ለማሳለጥ የተቋቋመው ምክር ቤቱ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የሚያግዙ የማማከር፣የማስተባበርና ችግሮችን የመለየት ብሎም የመፍትሄ አቅጣጫ የማስቀመጥ ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ ከተቋቋመ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ የተሰሩ ሥራዎች የገጠር ልማት ግቦችን ከማሳካት አንፃር ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውንም አንስተዋል።