ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሚካሄደው "ወርልድ ቴኳንዶ የአፍሪካ ፕሬዝዳንትስ ካፕ" ለአፍሪካ ቴኳንዶ ስፖርት እድገት የጎላ አበርክቶ ይኖረዋል - የአፍሪካ ቴኳንዶ ሕብረት ፕሬዝዳንት ኢዴ ኢሳካ

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 16/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከነገ ጀምሮ የምታስተናግደው "ወርልድ ቴኳንዶ የአፍሪካ ፕሬዝዳንትስ ካፕ" ለአፍሪካ ቴኳንዶ ስፖርት እድገት የጎላ አበርክቶ እንዳለው የአፍሪካ ቴኳንዶ ሕብረት ፕሬዝዳንት ኢዴ ኢሳካ ገለጹ፡፡

ዛሬ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ቴኳንዶ ሕብረት ጠቅላላ ጉባኤ ኢዴ ኢሳካን የሕብረቱ ፕሬዝዳንት አድርጎ በድጋሚ የመረጠ ሲሆን የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዳዊት አስፋውን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት ስድስት ምክትል ፕሬዝዳንቶች በመምረጥ ተጠናቋል፡፡

የአፍሪካ ቴኳንዶ ሕብረት ፕሬዝዳንት ኢዴ ኢሳካ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ጉባኤው የአፍሪካን ቴኳንዶ ስፖርት ለማሳደግ ወሳኝ የአመራር ለውጥ አድርጓል፡፡

ቴኳንዶ በአፍሪካውያን መካከል መቀራረብንና አብሮነትን የሚያንጸባርቅ እንዲሁም የባህል ልውውጥ የሚካሄድበት ትዕይንተ ስፖርት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአፍሪካ በቂ አትሌቶች ከሌሉ ሕብረቱ ህልውና የለውም ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተሳትፎዎችን ማሳደግ ትኩረታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ነገ የምታስተናግደው "የወርልድ ቴኳንዶ ፕሬዝዳንትስ ካፕ" ለአፍሪካ ቴኳንዶ ስፖርት እድገት የጎላ አበርክቶ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ይፋ የሚደረገው ዞናል የቴኳንዶ ውድድር በአፍሪካ እስካሁን ያልተደረገ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህም ለአህጉሪቱ ቴኳንዶ እድገት ገንቢ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ቴኳንዶ በተለይም ወጣቶች በብዛት የሚሰባሰቡበት ስፖርት በመሆኑ ለስፖርት ቱሪዝም የጎላ አበርክቶ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካን ቴኳንዶ ስፖርት በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ደረጃ ማሳደግ የሕብረቱ የቀጣይ የቤት ሥራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መክዩ መሀመድ፤ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቴኳንዶ ሕብረት በተጨማሪ ሌሎች ስፖርታዊ ክዋኔዎች እያስተናገደች ነው ብለዋል።

ሕብረቱ በአፍሪካ የቴኳንዶ ስፖርት ፈጣን እድገት እንዲያስመዘግብ የፕሬዝዳንት ኢዴ ኢሳካ ጥረት የላቀ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከነገ ጀምሮ በምታስተናግደው የወርልድ ቴኳንዶ ሕብረት ፕሬዝዳንትስ ካፕ ከ35 በላይ ሀገራት 250 ታዋቂ አትሌቶች ይሳተፋሉ ብለዋል።

በአፍሪካ የቴኳንዶ ስፖርት የወጣቶችን ሥነ ምግባር የሚያንጸባርቅ መሆኑን ገልጸው፤ የአፍሪካ ቴኳንዶ ሕብረት ከስፖርት ባለፈ የአፍሪካ ወጣቶችን መጻኢ ጊዜ አቅጣጫ የሚያስይዝ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ቴኳንዶ ሕብረት ምክትል ፕሬዝዳንት ዳዊት አስፋው በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቴኳንዶ ሕብረት በምክትል ፕሬዝዳንትነት መወከሏ ያላትን ተሳትፎ ወደ ውጤት ለመቀየር እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ሁለተኛዋ ባለጥቁር ቀበቶ ተፈታኞችን የምታቀርብ መሆኗን ገልጸው፤ ተሳትፎዋ ከዚህ በላይ ሊያድግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በአፍሪካ ተጽዕኖ መፍጠር የሚያስችል አቅም አለን ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከአምስት ሺህ በላይ በጥቁር ቀበቶ የምታስፈትን መሆኗንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም