የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የሚበለፅገው በጠንካራ የአየር ትስስር ሲደገፍ ነው -ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የሚበለፅገው በጠንካራ የአየር ትስስር ሲደገፍ ነው -ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 16/2017(ኢዜአ)፦የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የሚበለፅገው በጠንካራ የአየር ትስስር ሲደገፍ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለፁ።
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ አቪዬሽን ፎረም በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል እየተካሄደ ይገኛል።
በፎረሙ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፣የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግስቴ፣የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰውን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፥ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ኢትዮጵያ አስተማማኝ፣ዘላቂ እና ትስስር ያለው የአፍሪካ አቬሽን ለመፍጠር እየሰራች ነው።
በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ትልቁ እና በርካታ መዳረሻዎች እንዳሉት ጠቅሰው፤ ይህም አህጉራትን ለማገናኘት ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን ለማሳለጥ የአየር ትስስርን ማጠናከር ወሳኝ እንደሆነም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ ሎሜ፣ ሊሎንግዌ እና ኪሳንጋኒ ባሉ ማዕከሎች መስፋፋቱን ገልፀው፤ በዚህም የፓን አፍሪካ ቁርጠኝነትን እያሳየ መሆኑን አብራርተዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው፤ መንግስት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች መካከል ቱሪዝም አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ የአቪዬሽን ዘርፍ ትስስር ወሳኝ በመሆኑን በአፍሪካ መካከል ያለውን የእርስ በእርስ ትስስር ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፤ፎረሙ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ፣ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት እና መሰል ጉዳዮችን ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር እንደሚደረግ አመላክተዋል።