ቀጥታ፡

የሳዑዲ ልማት ፈንድ ለኢትዮጵያ ልማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ሚዚያዝያ 16/2017(ኢዜአ)፦ የሳዑዲ ልማት ፈንድ ለኢትዮጵያ ልማት የሚያደርገውን ድጋፍ በቀጣይነት አጠናክሮ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል።

በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ባለው የዓለም ባንክና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ስብሰባ እየተሳተፉ የሚገኙት የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ፥ ከሳዑዲ ልማት ፈንድ ዋና ስራ አስፈጻሚ
ሱልጣን አብዱልራህማን አልማርሻድ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይታቸውም፥ በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ቁልፍ ጉዳዮች እና የሳዑዲ ልማት ፈንድ በኢትዮጵያ ስለሚኖረው ተሳትፎ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።

ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ፥ የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ሂደትና ውጤቶች ላይ በዝርዝር ያስረዱ ሲሆን ማሻሻያው የግል ዘርፍ ተሳትፎን ያሳደገና የሃይልና ትራንስፖርት ዘርፉን ጨምሮ በመንግስት መሰረተ ልማት ዝርጋታ ያመጣውን ተጨባጭ ለውጥ አንስተዋል።

በቱሪዝም፣በማዕድንና በግብርናው ዘርፍ ዕምቅ አቅሞችን አሟጦ መጠቀም በየዘረፉ የተመዘገበውን እመርታም አስረድተዋል።

የሳዑዲ ልማት ፈንድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሱልጣን አብዱልራህማን አልማርሻድ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስመንት ምቹ ምህዳር ለመፍጠር የወሰደችውን ሪፎርምና የተመዘገበውን ውጤት አድንቀዋል።

ይህም ኢትዮጵያ በቀጣናውና በተቀረው አፍሪካ የትስስርና የልማት ስበት ማዕከልነቷን የሚያጎለብት መሆኑን ገልጸዋል።

የሳዑዲ ልማት ፈንድ የኢትዮጵያን ልማት በቀጣይነት ለመደገፍም ቁርጠኛ ስለመሆኑ አረጋግጠዋል።

የስራ ሃላፊዎቹ የሁለቱን ሀገራት የረጂም ጊዜ የዘለቀ ጥብቅ የሁለትዮሽ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የጋራ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከርም ተስማምተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም