ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዳዊት አስፋው የአፍሪካ ቴኳንዶ ሕብረት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 16/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዳዊት አስፋው የአፍሪካ ቴኳንዶ ሕብረት ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን ተመርጠዋል።

የአፍሪካ ቴኳንዶ ሕብረት ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ አካሂዷል።

በጉባኤው ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መክዩ መሀመድ፣ የአፍሪካ ቴኳንዶ ሕብረት ፕሬዝዳንት ኢዴ ኢሳካ፣ የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዳዊት አስፋው እና የሕብረቱ አባል ሀገራት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የሕብረቱ ጠቅላላ ጉባኤ ኢዴ ኢሳካን ፕሬዝዳንት አድርጎ በድጋሚ መርጧል።

የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዳዊት አስፋውን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት ስድስት ምክትል ፕሬዝዳንቶች ተመርጠዋል።


 

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መክዩ መሀመድ በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቴኳንዶ ሕብረት በተጨማሪ ሌሎች ስፖርታዊ ክዋኔዎች እያስተናገደች ነው ብለዋል።

የአፍሪካ ቴኳንዶ ሕብረት በአፍሪካ የቴኳንዶ ስፖርት ፈጣን እድገት እንዲያስመዘግብ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ ሳምንት በምታስተናግደው የአፍሪካ ቴኳንዶ ሕብረት ፕሬዝዳንቶች ዋንጫ ከ35 በላይ ሀገራት 250 ታዋቂ አትሌቶች ይሳተፋሉ ብለዋል።

እንዲሁም ቴኳንዶ ከስፖርትም በላይ የወጣት አፍሪካውያንን ምኞትና ፍላጎት ባህላዊ ትዕይንት መሆኑን ገልጸዋል።

በአፍሪካ የቴኳንዶ ስፖርት የወጣቶችን ስሜትና ሥነ ምግባር ሲያንጸባርቅ ይታያል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ጠንካራ፣ ሁሉን አቀፍና ጤናማ ማህበረሰብ ለመገንባት ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም