በክልሉ ግብርናውን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ግብርናውን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ

ሚያዝያ 16/2017(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ግብርናውን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ተገልጿል።
የኦሮሚያ ክልል የግብርና ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ሶስተኛ ጉባዔ በክልሉ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት እየተካሄደ ይገኛል።
በጉባዔው የክልሉ ፕሬዚዳንትና የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሽማልስ አብዲሳ፤ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) እና ሌሎች የፌዴራል እና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ በወቅቱ እንደተናገሩት በክልሉ ግብርናውን ከተለመደው አሰራር በማላቀቅ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው።
ይህንኑ ሂደት ለማሳለጥ የተቋቋመው ምክር ቤቱ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የሚያግዙ የማማከር፣ የማስተባበርና ችግሮችን የመለየት ብሎም የመፍትሄ አቅጣጫ የማስቀመጥ ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ምክር ቤቱ ከተቋቋመ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ የተሰሩ ስራዎች የገጠር ልማት ግቦችን ከማሳካት አንፃር ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በግብርና ላይ የተከናወነው የሽግግር ስራ ቀደም ሲል ከውጪ ሲገባ የነበረውን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ ማምረት ማስቻሉን አስታውሰዋል።
በክልሉ ግብርናውን በማዘመን ረገድም ትልቅ ለውጥ እየመጣ መሆኑን አስረድተው በክልሉ በትራክተር የሚታረስ መሬት ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ጨምሯል ብለዋል።
ግብርናው እየዘመነ በመምጣቱም ወጣቶች የግብርና ስራ ላይ ያላቸው ተሳትፎ እንዲያድግ እድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸው በክልሉ እየታየ ያለውን ለውጥ ለማሳካት የግብርና ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤቱ ትልቅ ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በመድረኩ እስካሁን የተገኙ ውጤቶችን የማጠናከር እና ቀሪ ግቦችን ለማሳካት በሚደረጉ ስራዎች ላይ በጥልቀት ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል።