አፍሪካውያን ዘመኑን የዋጀ ላቦራቶሪ በማሟላትና ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር አቅምን ማጠናከር ይገባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካውያን ዘመኑን የዋጀ ላቦራቶሪ በማሟላትና ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር አቅምን ማጠናከር ይገባቸዋል
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 15/2017(ኢዜአ)፦ አፍሪካውያን ዘመኑን የዋጀ ላቦራቶሪ በማሟላትና ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር አቅምን ማጠናከር ይገባቸዋል ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ መንበር ሰልማ ማሊካ አፍሪካውያን የጤና ችግሮችን በራሳቸው አቅም ለመፍታት አህጉራዊ የፋይናንስ አቅማቸውን ማጠናከርና ከአጋሮች ጋር መተባበር አለባቸው ብለዋል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆየው የሩሲያ-አፍሪካ የንጽህናና በሽታዎች ስርጭት የአደጋ ጊዜ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን የመጀመሪያ ስልጠናና ሴሚናር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ የ15 የአፍሪካ ሀገራት ባለሙያዎች የአደጋ ጊዜ ፈጣን ምላሽ እና በጥናት ላይ የተመሰረተ አገልግሎት መስጠት የሚችሉበት ስልጠና ይወስዳሉ፡፡
ከመርሀ ግብሩ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ የጤና አገልግሎትን ማዘመን የሚያስችል ዘመናዊ የተንቀሳቃሽ ላቦራቶሪ ድጋፍ ርክክብ ተደርጓል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠርና መከላከልን ጨምሮ ሌሎች የጤና ምርምር ተቋማት መገኛ ናት፡፡
የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት እና ሌሎች የላቦራቶሪና ምርምር ተቋማት እንዳሏት ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም እነዚህን የላቦራቶሪ እና የምርምር ተቋማት አቅም በማጎልበት እንዲሁም አዳዲስ ተቋማትን በመፍጠር የበሽታ መከላከል አቅምን ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሩሲያን ጨምሮ ከሀገራት ጋር የበሽታ መከላከል አቅምን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን በትብብር እያከናወነች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አፍሪካውያን ዘመኑን የዋጀ ላቦራቶሪ በማሟላትና ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር አቅማቸውን ማጠናከር ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
ሩሲያ ድጋፍ ያደረገችው ተንቀሳቃሽ ላቦራቶሪ ከ300 በላይ በሽታዎችን የመለየት አቅም ያለው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ እስካሁን 33 ላቦራቶሪዎች እንዳሏት ገልጸው፤ በቀጣይ ወደ 40 ለማሳደግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡
በአፍሪካ ወረርሽኝ በሚከሰትበት ጊዜ በፍጥነት ተንቀሳቅሶ ወደ ኅብረተሰቡ በመድረስ አገልግሎት መሥጠት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ተንቀሳቃሽ ላቦራቶሪው ከኢትዮጵያ አልፎ ለጎረቤት ሀገራት አገልግሎት በመስጠት በቀጣናው ጠንካራ ትስስር መፍጠር ያስችላል ብለዋል፡፡
በሩሲያ የፌዴራል የደንበኞች መብት ጥበቃ እና ሰብዓዊ ደህንነት ቁጥጥር አገልግሎት ኃላፊ አና ዩ ፖፖቫ ሩሲያና ኢትዮጵያ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ በጤናው መስክም በትብብር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
አፍሪካውያን በሽታ የመከላከል አቅማቸውን በራሳቸው ማጎልበት ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡
የዛሬው መድረክ አፍሪካ ወረርሽኝ ሲከሰት በራሷ ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅሟን የሚያጎለብት መሆኑን ገልጸው፤ የሩሲያ መንግሥት ድጋፉን እንደሚያጠናክር ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ መንበር ሰልማ ማሊካ በበኩላቸው ሩሲያ ያዘጋጀችው የአቅም ግንባታ ስልጠና ለአፍሪካ የጤና ስርዓት መጠናከር ያላትን የድጋፍ ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አፍሪካውያን አህጉራዊ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከልን ጨምሮ ሌሎች አፍሪካውያን ተቋማት አቅማቸውን በማጠናከር የዜጎችን ጤና ማረጋገጥ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
አባል ሀገራቱ የጤና ችግሮቻቸውን መፍታት የሚችሉበት አፍሪካዊ መፍትሔ እንዳለ የገለጹት ምክትል ሊቀ መንበሯ፤ አህጉራዊ የፋይናንስ ተቋማትን ማጠናከር እና ከአጋሮች ጋር በትብብር መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ድንበር ተሻጋሪ የበሽታ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የጋራ ጥረት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ሩሲያ የአፍሪካን የበሽታ መከላከል አቅም ለማሳደግ ድጋፍና ትብብሯን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።