የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በብጹዕ ወቅዱስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሕልፈት የተሰማውን ሐዘን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በብጹዕ ወቅዱስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሕልፈት የተሰማውን ሐዘን ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 15/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በብጹዕ ወቅዱስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሕልፈተ ሕይወት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገልጿል።
ጉባኤው በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በ88 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉ ቢሆንም በህይወት ዘመናቸው ራሳቸውን ለእግዚአብሄር እና ለቤተክርስቲያን ክብር የሰጡ ናቸው።
ለመላው የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ለሰጡት ታላቅ መንፈሳዊ አገልግሎት እና አመራር እንዲሁም ለዓለም ሰላም ላበረከቱት የላቀ አበርክቶ ዘወትር ሲታወሱ ይኖራሉም ብሏል በመግለጫው።
በተለይ በዓለም የጦርነት እና የግጭት እንቅስቃሴ ቆሞ ሕዝቦች በሰላማዊ የወንድማማች ትብብር በመከባበር እና በአንድነት ይኖሩ ዘንድ በግጭት ውስጥ ያሉትን የተለያዩ አካላት ዝቅ ብለው የለመኑ፤ ለዕርቅ እና ለሰላም በብዙ የደከሙና የጣሩ ታላቅ አባት ነበሩ ብሏል።
ይህን ታላቅ አርአያነታቸውን ሁላችንም የሃይማኖት መሪዎች እና አገልጋዮች ልንከተለውና ለዓለም ሰላም ትኩረት በመስጠት የበኩላችንን አወንታዊ አስተዋጽኦ ልናበረክት ይገባል ሲልም ጉባኤው በመግለጫው አንስቷል።
በብጹዕ ወቅዱስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሕልፈተ ሕይወት ምክንያት ከፍተኛ ሀዘን ውስጥ ለሚገኙ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ መሪዎች፣ አገልጋዮች እና ምዕመናን በሙሉ አጽናኙ እግዚአብሄር ልባዊ መጽናናትና ጽናትን እንዲሰጥልን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከልብ ይመኛል ሲልም ገልጿል።