ቀጥታ፡

ሞገደኛ የፋሲካ ሰንጋ ...

(ከፍቅርተ ባልቻ)

ከዘንድሮ የበዓለ ትንሳዔ አይረሴ ገጠመኞች አንዱ ነው- ለዕርድ አሻፈረኝ ያለው በሬ። ነገሩ ወዲህ ነው። በለሚኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 18ተኛው ፕላኔት የጋራ መኖሪያ ግቢ ነዋሪዎች መካከል ስድስት ሰዎች የፋሲካ ቅርጫ ስጋ ለመቃረጥ ይስማማሉ።

እናም የቅዳም ስዑር ዕለት(የፋሲካ ዋዜማ) ወደ ካራ ገበያ አመሩ። አቅማቸውን ያገናዘበ በሬ 68 ሺህ ብር ሸምተው ሰንጋቸውን እየነዱ ወደ መንደራቸው ጉዞ ጀመሩ።

ይሁንና ድንገት በሬው ደነበረ። ለያዥ ለገናዥ አስቸገረ። አመለጠ። ያዘው ያዘው የሚል ድምጽ ብቻ ሆነ። ባለሰንጋዎቹ የበሬ ኮቴ ተከትለው መንከራተት ሆነ። ሰውዎችም፤ በሬውም መደንበር ተያያዙት።

ጀንበር ስታዘቀዝቅ አመሻሽ ላይ በቁጥጥር ስር ውሎ ወደ’ጋራ መኖሪያ መንደር ተወሰደ።

አጠባብ ላይ ለእርድ ተፈርዶበት አራጆች ተሰባሰቡ። ሰንጋውን ለመቃረጥ ሁሉም ተፍ ተፍ እያለ ነበር። ሰንጋው ግን አደገኛ ነበር። በገመድ የያዘውን ሰው ከመሬት ደባልቆ(ደቁሶ) በድጋሚ አሻፈረኝ ብሎ ፈረጠጠ አመለጠ።

በሬው ሲያመልጥ መንደሩ ተራወጠ። ከጣፋጭ እንቅልፍ ላይ ተነስተው ወደ ቅርጫ የተሰባሰቡ ቤተሰቦች በየፊናው በሬ ፍለጋ ኳተኑ። በሬ ሆይ የት ይገኝ። ሌሊቱ የአህያ ሆድ መሰለ። ምን ዋጋ አለው በሬ ቢፈለግ የውሃ ሽታ ሆነ።

68 ሺህ ብር አዋጥተው የተገዛው በሬ መታረጃው ሰዓት ማለፉ ብቻ ሳይሆን ጭራሽኑ ጠፋ።

አንዱ አንዱን እያጽናና ተስፋ በመቁረጥ ስሜት በዓሉን እንዴት እናሳልፍ እያሉ ሃሳብ እያወጡ እያወረዱ ሳለ ድንገት የምስራች መጣ።

ከወረዳ 06 ፖሊስ ጣቢያ የተደወለ ስልክ የእናንተ ከሆነ ከማስረጃ ጋር በሬያችሁን ውሰዱ የሚል ብስራት አመጣ። በፍጥነት ፖሊስ ጣቢያ ከተፍ ሲሉ እውነትም አደገኛው በሬ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ነበር። ሞገደኛውን በሬ ይዘው ወደ መንደራቸው ተመለሱ። ምንም ቢጠነቀቁም ቅሉ በሬው ግን አሻፈረኝ ከማለት አልቦዘነም።

ለዕሁድ ንጋት የታሰበው በሬ ዕሁድ አመሻሽ ‘አንገት’ ሰጠ። ለአንድ ቀን መንደሩንም፣ ቀየውንም ያመሰው፣ ደንብሮ ያስደነበረው ሞገደኛው ሠንጋ ወደቀ።

18ተኛው ፕላኔት የጋራ መኖሪያ ብሎክ 1119 ነዋሪአቶ ይገዛል አረጋ ከበሬ ገዥዎችና ከዕርድ ስርዓት አስተባባሪዎች አንዱ ነበሩ። ገጠመኙን ሲተርኩ እንደነገሩን ከሌሊቱ 8 ሰዓት ወደ ዕርድ ቦታ ሲወስዱት በሬው በማስቸገሩ እርሳቸውም በሬውን ላለመልቀቅ ሲታገሉ በአንድ እጃቸውና ሁለት እግሮቻቸው ላይ ጉዳት አድርሶ ተሰወረ።

ከበዓል ወቅት ጥንቃቄዎች አንዱ የእርድ ስርዓት እንደሆነ አቶ ይገዛል ከተሞክሯቸው ያነሳሉ። የዕርድ ሰዓት ከሌሊት ይልቅ ማለዳ ላይ ቢከወን የተሻለ ነው ሲሉ ይመክራሉ። ሌሊት በመሆኑ የጠፋውን በሬ ፈልጎ ለመያዝ አስቸጋሪ አድርጎት ነበር ይላሉ። የሌሊት እርድ ለአደጋም፣ ለኪሳራም የሚዳርግ በመሆኑ ሌሎችም ከእኛ ተሞክሮ ይማሩ ሲሉ መልዕክት አስተላለፈዋል።

በሬውን ያስረከባቸውን የወረዳ ስድስት ፖሊሲ ጣቢያም ያመሰግናሉ። የጠፋውን በሬ ይዘው ለፖሊስ ያስረከቡትን የቦሌ አራብሳ ጨርቆስ አካባቢ ነዋሪዎች ናቸው። አቶ ይገዛል ኢትዮጵያዊ እሴትን በተግባር ያሳዩትን የአራብሳ ጨርቆስ አካባቢ ነዋሪዎች ሀቀኝነትም አድንቀዋል።አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም