1 ሺህ 382 አዳዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል -አገልግሎቱ - ኢዜአ አማርኛ
1 ሺህ 382 አዳዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል -አገልግሎቱ
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 15/2017 (ኢዜአ)፦ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ 1 ሺህ 382 አዳዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ታዬ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፥ ለውጡን ተከትሎ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ተደራሽነት ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል።
በተለይም አገልግሎቱ በገጠር ከተሞችና መንደሮች እንዲዳረስ የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶች አምጥተዋል ብለዋል።
ለአብነትም ባለፉት የለውጥ ዓመታት 1 ሺህ 382 አዳዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።
ቆጣሪ ገብቶላቸው የሚገለገሉ ደንበኞች ከ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ያልዘለለ እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት ቁጥሩን ከ 5 ሚሊዮን በላይ ማድረስ መቻሉ ትልቅ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽፋኑ ይበልጥ ሊሰራበት የሚገባው ነው ያሉት አቶ መላኩ፥ በተለይም ከግሪድ ርቀው የሚገኙ አካባቢዎች የጸሃይ ኃይል በመጠቀም የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ የማድረጉ ሥራ አበረታች ውጤት እየተገኘበት ነው ብለዋል።
መሰረተ ልማቶች ረጅም ጊዜ ያገለገሉ ከመሆኑም በላይ ወቅቱን የዋጀ አለመሆኑ ለአገልግሎት መቆራረጥ እና ለደንበኞች ቅሬታ ምንጭ እንደሆነ መለየቱን ጠቅሰዋል።
ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀትም አገልግሎቱ ከሚሰበስበው ገቢ እንዲሁም ከልማት አጋሮች የሚገኘውን ፋይናንስ በመጠቀም በዋና ዋና ከተሞች ኔትወርክ ማሻሻያና መልሶ ግንባታ ሥራዎች በስፋት እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ አዳማ፣ መቀሌ፣ ባህዳር እና ጅማ በመሳሰሉ ከተሞች ላይ የመጀመሪያው ምዕራፍ የኔትወርክ ማሻሻያ እና መልሶ ግንባታ ሥራው መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ወላይታ ሶዶ፣ ሀረር፣ ሻሸመኔ፣ ደብረ ማርቆስ ጎንደርና ኮምቦልቻን ጨምሮ በስድስት ከተሞች ላይ የተጀመረው የኔትወርክ ማሻሻያ እና መልሶ ግንባታ ሥራ እየተገባደደ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሥራ አስፈጻሚው እንዳሉት፤ የኔትወርክ ማሻሻያ እና መልሶ ግንባታ ሥራዎች ተጠናቀው በተሟላ ቁመና ወደ ሥራ ሲገባ ለደንበኞች አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ያስችላል።
የደንበኞች እርካታን የሚያሳድጉ አገልግሎቶችን ለመስጠት ተቋሙ ጥናት ላይ የተመሰረቱ የመፍትሄ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑንም ገልጸዋል።
የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሲከሰቱ የሞባይል መተግበሪያን በመጠቀም ጥቆማ የሚሰጥበት አሰራር መዘርጋቱን የገለጹት አቶ መላኩ፤ ደንበኞች ተሳትፎ በማድረግና ጥቆማ በመስጠት የመፍትሄ አካል እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።