ቀጥታ፡

የቡናን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ ለጥራት ትኩረት ተሰጥቷል-ባለስልጣኑ

ሚዛን አማን፣ሚያዚያ 15/2017 (ኢዜአ)፦የቡናን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ ለጥራት ትኩረት መሰጠቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታጋይ ኑሩ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የቡናን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ የቡናን ዝርያ ከማሻሻል በተጨማሪ ከምርት አሰባሰብ እስከ ሽያጭ ድረስ ያለውን ሰንሰለት ጥራት ለማስጠበቅ ትኩረት ተሰጥቷል።

በምርት ዘመኑ ለገበያ ከቀረበው ከ299 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው፥ አምና በተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነጻጸር ብልጫ እንዳለው አንስተዋል።

የቡና ጥራት አጠባበቅ ሥርዓትን ለማጠናከር በቡና ልማትና ምርት አያያዝ ላይ ለአርሶ አደሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን ከመስጠት ባለፈ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ለማስፋፋት ከምርምር ተቋማት ጋር በትብብር መሰራቱን አንስተዋል።

የቡናን ዋጋ ከፍ የሚያደርጉ የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ጠቁመው፥ ለአብነትም ደረጃ አራትና እና ደረጃ አምስት የቡና ምርቶችን ከገበያ ማስወጣት መጀመሩን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የጥራት ማሻሻያ ፓኬጅ ተቀርጾ ለክልሎች የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።

የጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል የቡና አያያዝ ተመራማሪ አቶ ከሊፋ ናስሮ በበኩላቸው፥ ማዕከሉ የኢትዮጵያን የቡና ምርታማነት የሚያሳድጉ የምርምር ሥራዎችን በማፍለቅ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የሚሆንበትን አሰራር ተግባራዊ ማድረጉን ገልጸዋል።

ለአካባቢ ተስማሚ የሆነ የቡና ዝርያን ከማስፋፋት ጀምሮ በምርት አሰባሰብ ሂደት ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን በቅንጅት በመፍታት የቡናን ጥራት ለማስጠበቅና በዋጋ ተወዳዳሪ ለመሆን ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚከናወኑም አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ለቡና ልማት ያላትን ምቹ ሥነ ምህዳር በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ በምርምር የሚገኙ የቡና ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ከማድረስ ባሻገር የሚደረገው ሙያዊ ድጋፍ መጠናከር እንዳለበትም መክረዋል።

የጥራት ደረጃን ጠብቆ ምርታማነትን ማሳደግ ከተቻለ አሁን እየታየ ያለው የቡና ዋጋ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያን በዘርፉ የዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ያደርጋታል ነው ያሉት ።

ኢትዮጵያ በዓመት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የቡና ምርት እንደምትሰበስብ ከባለሥልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም