በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ359 ሺህ በላይ ዜጎች የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ተጠቃሚ ሆነዋል- ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ359 ሺህ በላይ ዜጎች የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ተጠቃሚ ሆነዋል- ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 15/2017 (ኢዜአ):- በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ከ359 ሺህ በላይ ዜጎች የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ተጠቃሚ መሆናቸውን የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ዕቅድ አፈፃፀማ ግምገማ ተካሂዷል።
በግምገማው ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ከሰለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት፣ ከሥራ ገበያው ፍላጎት እና ከአገልግሎት አሰጣጥ አኳያ የተከናውኑ ሥራዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፥ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 359 ሺህ 291 ዜጎችን በውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።
ካለው የሥራ ገበያ ፍላጎት አኳያ አቅርቦት እና ጥራት ላይ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ውጤቱን ለማላቅ እና የዜጎችን ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን አመልክተዋል።
በዘርፉ በመንግስትና በግል ተቋማት የሚሰጠው ሥልጠና የሥራ ገበያውን ፍላጎት የሚመልስ እና ፍላጎትና አቅርቦቱን ማጣጣም የሚያስችል መሆኑን የማረጋገጥ እንዲሁም ማነቆዎችን መፍታትና ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነም ጠቁመዋል።
በዘርፉ የተጀመረው የዜጎችን መብት ደህንነትና ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ሥራ እንዲሁም ህገ-ወጥነትን መከላከልና ህግና ስርዓትን ማስከበር በልዩ ሁኔታ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ሚኒስትሯ።
ለዚህም በየደረጃው የሚመለከታቸው ባለድርሻ እና አስፈፃሚ አካላት ሁሉን አቀፍ ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።