ቀጥታ፡

በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች የክልሉን እድገት የሚያፋጥኑና የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው

አሶሳ፤ሚያዚያ 14/2017(ኢዜአ)፦በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች የክልሉን እድገት የሚያፋጥኑና የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ በአሶሳ ከተማ የሚገኙ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ዛሬ ጎብኝተዋል።

በእዚህ ወቅት እንደገለፁት፥ በክልሉ በመከናወን ላይ ያሉ የልማት ሥራዎች የክልሉን እድገት የሚያፋጥኑና የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው።

በሌማት ትሩፋት መርሀግብር እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፥ልማቱን በመደገፍና በማጠናከር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ ይገባል።

በተለይ በእንስሳት እርባታ ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች አበረታች በመሆናቸው የእንስሳት ተዋፅኦ ምርታማነት እንዲጨምር የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።

በአሶሳ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማትም የከተማዋን የወደፊት ዕድገት ታሳቢ ያደረገ እና ለኢንቨስትመንት ምቹ እንድትሆን የሚያደርግ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ልማቱ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ የቱሪዝም ፍሰት እንዲጨምር ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰው፥የልማት ስራዎቹ የክልሉን እድገት ከማፋጠን ባለፈ ህዝብን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ብለዋል።

ሚኒስትሩ በተጨማሪም በአሶሳ ከተማ በ469 ሚሊዮን ብር እየተገነባ ያለውን የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ግንባታ ማዕከል ጎብኝተዋል።

ማዕከሉ ፈሳሽ ቆሻሻን በማጣራት ለልማት ሥራ ለማዋል እና ዘመናዊ የቆሻሻ አወገጋድ ስርዓት እንዲፈጠር ያግዛል ብለዋል።

ይህም አሶሳ ከተማን ጽዱ እና ውብ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ሲሉ አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም