ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ያላቸውን ትብብር እንደሚያጠናክሩ ገለጹ

አዲስ አበባ ፤ ሚያዝያ 14/2017 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ያላቸውን የጋራ ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ።

በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም ባንክ ግሩፕ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ የፀደይ ወቅት ስብሰባ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።

ቡድኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አማካሪ ተክለወልድ አጥናፉ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እና ሌሎች ልዑካንን ያካተተ ነው።


 

ልዑኩ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ጋር ተወያይቷል።

ውይይቱ በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሞች እና ሁለቱ ወገኖች በትብብር መስራት በሚችሉባቸው መስኮች ላይ ያተኮረ ነው።

ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ፈተናዎች ሳያግዷት የወሰደቻቸው ቁልፍ የሪፎርም አጀንዳዎች እና በማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ላይ ያስመዘገበችውን አመርቂ ለውጥ አድንቀዋል።

የአይኤምኤፍ ልዑክ በቅርቡ በኢትዮጵያ በነበረው የፕሮግራም ግምግማ ላይ የዋጋ ንረት መቀነስ፣ ጠንካራ የፊስካል ዲሲፒሊን እና የገቢ አሰባሰብ አቅምን ማሳደግን ጨምሮ መልካም የሚባሉ ለውጦች መታየታቸውን አመልክተዋል።

ድርጅቱ ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራሙ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ አይኤምኤፍ ለኢትዮጵያ የሪፎርም አጀንዳ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሪፎርሙ ኢኮኖሚውን ለማጠናከር እና ለማዘመን፣ አዲስ የእድገት እድሎችን ለመክፈት፣ የግሉ ዘርፍ ስራ እድል ፈጠራን ጨምሮ ያለውን የኢኮኖሚ ተሳትፎ ለማሳደግ እና የኢትዮጵያውያንን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችል ነው ብለዋል።

ሁለቱ ወገኖች በውይይታቸው የሪፎርም ስራውን ይበልጥ በማጠናከር ኢንቨስትመትን ለመሳብ ምቹ የንግድ ሁኔታ መፍጠር በሚቻልባቸው ቀጣይ እርምጃዎች ላይ ሀሳቦች ተለዋውጠዋል።

በውይይቱ ላይ አይኤምኤፍ ለኢትዮጵያ እድገት እና ልማት የሚያደርገው ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጹን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የዓለም ባንክ ግሩፕ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ የፀደይ ወቅት ስብሰባ እስከ ሚያዚያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም