ቀጥታ፡

መንግስት ፍልሰተኞች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት እያከናወነ ያለው ተግባር የሚደነቅ ነው - ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 14/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መንግስት የተለያዩ ሀገራት ፍልሰተኞች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት በትኩረት እየሰራ መሆኑ የሚደነቅ ተግባር መሆኑን በኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ከፍተኛ የፕሮግራም ኃላፊ ሚሞሪ ምዋሌ ገለጹ።

የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ፍልሰተኞች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት በትብብር እየሰራ መሆኑን ኃላፊዋ ገልጸዋል።

ኃላፊዋ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት በፍልሰተኞች አስተዳደር ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በአጋርነት ይሰራል።

ኢትዮጵያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ፍልሰተኞችና የፍልሰተኞች ደህንነት ጉዳይን በህግ እና በስርአት እንዲመራ እየሰራች መሆኑ የሚደነቅ ተግባር ነው ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት እና የኢትዮጵያ መንግስት በፍልሰተኞች ዙሪያ በትብብር እየሰሩ በመሆኑ ሌሎች ባለድርሻና አጋር አካላትም በቅንጅት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ከኢትዮጵያ መንግስት የፍልሰተኞች ደህንነት ጥበቃና ውጤታማ የፍልሰተኞች አስተዳደር ላይ በትብብር ለመስራት የአምስት አመት ሀገር አቀፍ የኮሙኒኬሽንና የጋራ ስትራቴጂክ እቅድ በቅርቡ ይፋ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ድርጅቱ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የጋራ ስትራቴጂክ እቅድ መሰረት የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰራ ገልፀዋል።

በተጨማሪም ድርጅት ለስደት ተመላሾች ጊዚያዊ የማቆያ ማዕከል ከማዘጋጀት ጀምሮ መልሶ ለማቋቋም ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም ህገወጥ ስደትን ለመከላከል ህብረተሰቡን የማስገንዘብና ህጋዊ መንገድ እንዲጠቀሙ ለማድረግ እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም