በወልቂጤ ከተማ ከ185 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የዘመናዊ ቄራ ግንባታ ሥራ እየተከናወነ ነው

ወልቂጤ፤ ሚያዚያ 14/2017(ኢዜአ)፡-በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ከ185 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የዘመናዊ ቄራ ግንባታ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማው ጥራቱን በጠበቀ መልኩ በኤክስፖርት ስታንዳርድ አገልግሎት የሚሰጥ ዘመናዊ የቄራ ግንባታ እየተካሄደ ነው።

የከብቶችን ጤንነት በአግባቡ መርምሮ ከእጅ ንኪክ ነጻ በሆነ መልኩ ዘመናዊ የእርድ አገልግሎት የሚሰጥ ቄራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከተማዋ ለአዲስ አበባ ያላት ቅርበት እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀምና የአካባቢውን የሥጋ ምርት ዕሴት በመጨመር  ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ታስቦ የግንባታ ሥራው መጀመሩን ተናግረዋል።

የፕሮጀክቱ ግንባታ ሥራ ከተጀመረ ሦስት ዓመታት ቢያስቆጥርም በተለያዩ ምክንያቶች በመዘግየቱ ቅሬታዎች ሲነሱ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ ችግሩን በመፍታት ለቀጣይ ዓመት ለአገልግሎት ለማብቃት ታቅዶ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ከንቲባው ገልጸዋል።

ለቄራ ግንባታ ፕሮጀክት 185 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞለት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፣ ቄራው ለክርስቲያንና ሙስሊም የእርድ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም የግንባታ ሥራው በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

የግንባታ ሥራው ሲጠናቀቅ ጥራት ያለውና ከብክለት የጸዳ የእርድ አገልግሎት በመስጠት የዜጎችን ጤና ለመጠበቅና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ያለው ፋይዳ የላቀ ነው ብለዋል።

በአካባቢው በእንስሳት እርባታና ማደለብ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች በተለይ ሀገራዊ የሌማት ትሩፋት ኢኒሺቲቭ በመጀመሩ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፣ የቄራው መገንባት ይህንን ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያሳድገው ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱን ለአገልግሎት ለማብቃት በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ መሆኑንና በአሁኑ ወቅትም ግንባታው ከ78 በመቶ በላይ መድረሱን የተናገሩት የጉራጌ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ታምራት ውደማ ናቸው።


 

በቀን እስከ 500 ከብት የእርድ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የሚገነባው ቄራ ከአዲስ አበባ ያለውን ርቀት ታሳቢ በማድረግ እየተገነባ መሆኑንም ገልፀው አቅም ያላቸው ባለሀብቶች  የሥጋ ምርትን ወደውጭ ኤክስፖርት ማድረግ የሚችሉበት ሁኔታ ታሳቢ መሆኑንም አመልክተዋል።   

አቶ ታምራት እንዳሉት በአሁኑ ወቅት የሴፍቲ ታንክን ጨምሮ ቀሪ የግንባታ ሥራዎችን የማጠናቀቅ ሥራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይ የማሽኖች ግዢ በመፈጸም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ለአገልግሎት ለማብቃት ይሰራል ብለዋል።

በከተማው እየተገነባ ያለው ዘመናዊ ቄራ በ5 ሄክታር መሬት ላይ ማረፉንና የግንባታ ሥራውም እየተጠናቀቀ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ግንባታውን እያከናወነ ያለው የፋሩቅ ተሰማ ሕንጻ ሥራ ተቋራጭ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፋሩቅ ተሰማ ናቸው። 


 

ቄራው የክርስቲያንና የሙስሊም እርድ አገልግሎት በተቀናጀ መንገድ በተለያዩ ክፍሎች የሚከናወንበት መሆኑን ጠቁመዋል።

የማረጃ ክፍሎች፣ የእርድ እንስሳት ጤና መፈተሻ እንዲሁም ደምና ሌሎች ተረፈምርቶች አካባቢውን በማይበክሉበት ሁኔታ የሚወገዱበት ሴፍቲ ታንክና ሌሎች የግንባታ ሥራዎች በአሁኑ ወቅት በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም