የማንችስተር ሲቲ እና አስቶንቪላ ተጠባቂ መርሃ ግብር - ኢዜአ አማርኛ
የማንችስተር ሲቲ እና አስቶንቪላ ተጠባቂ መርሃ ግብር
አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 14/2017(ኢዜአ)፡- በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ34ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ማንችስተር ሲቲ ከአስቶንቪላ ዛሬ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በኢትሃድ ስታዲየም ይደረጋል።
ማንችስተር ሲቲ በ58 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ አስቶንቪላ በ57 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሁለቱ ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ ብርቱ ፉክክር እያደረጉ ይገኛሉ።
ለቡድኖቹ ማሸነፍ ለሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ህልማቸው ወሳኝ የሚባል ነው።
ነገ በሌላኛው የ34ኛ ሳምንት መርሃ ግብር አርሰናል ከክሪስታል ፓላስ ይጫወታል።
ሁለቱ ጨዋታዎች በሳምንቱ አጋማሽ እንዲደረጉ የተወሰነው ክሪስታል ፓላስ ከአስቶንቪላ እና ማንችስተር ሲቲ ከኖቲንግሃም ፎረስት በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በሚያደርጉት የኤፍኤ ካፕ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ምክንያት ነው።
ኖቲንግሃም ፎረስት ከብሬንትፎርድ ጋር ሊያደርገው የነበረው የ34ኛ ሳምንት ጨዋታም ወደ ቀጣዩ ሳምንት መዘዋወሩን የእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር አስታውቋል።
ሌሎቹ መርሃ ግብሮች በተያዘላቸው ጊዜ የፊታችን ቅዳሜ እና እሁድ ይደረጋሉ።