በክልሉ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ አመራሩ የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ መወጣት አለበት - አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዳማ፤ ሚያዝያ 14/2017(ኢዜአ)፦ በክልሉ የህዝብ የልማትና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥያቄዎችን ለመመለስ በየደረጃው ያለው አመራር የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ መወጣት እንዳለበት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ አሳሰቡ።

የኦሮሚያ ክልል የዘጠኝ ወራት የመንግስትና የፓርቲ የስራ ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ በአዳማ ገልማ አባገዳ በመካሄድ ላይ ይገኛል።


 

ፕሬዝዳንቱ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት የመድረኩ ዓላማ ያለፉት ዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ውስጥ የተሳኩ ስራዎችና የታዩ ክፍተቶችን በአግባቡ በመፈተሽ ለቀጣይ የጋራ አቅጣጫ ማስቀመጥ ነው።

አራተኛው ሩብ ዓመት የበጀት ዓመቱን የልማት ስራዎች የምናጠናቅቅበት ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ከስራ አፈፃፀም ግምግማው በተጓዳኝ የ2018 በጀት ዓመት የልማት ዕቅድ ዝግጅት ያለበትን ሁኔታ በአግባቡ በመፈተሽ ልናሳካ ያሰብነውን ግብ ያማከለ መሆኑ የሚፈትሽበት መድረክ ነው ብለዋል።

አመራሩ የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ በመፈፀም የህዝቡን የመልማት ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችል አመራር መስጠት መቻል አለበት ብለዋል።

በተለይም አሁን የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በማለፍና በየደረጃው ያለውን አመራር በማስተባበር ለህዝቡ የልማት፣ የአገልግሎትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በተለይም የተሰጠውን ተልዕኮ የሚመጥን ብቃት፣ ስነ ምግባር ያለውና ተልዕኮውን መፈፀም የሚችል እንዲሁም ውስብስብ ችግሮችን ማለፍና ዕቅዳችንን ማሳካት የሚችል አመራር መገንባት አለብን ነው ያሉት።

በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ በበኩላቸው በሶስተኛው ሩብ ዓመት የተሰሩ ስራዎች የተሻለ ውጤት የተገኘባቸው ናቸው ብለዋል።

በተለይም በፓርቲ ስራ አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት ውጤታማ እንዲሆን፣ መስሪያ ቤቶችን በመገንባትና ቀልጣፋ አገልግሎት ህዝቡ እንዲያገኝ ከማድረግ አኳያ የተሻለ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

የመልካም አስተዳደር እጦት ችግርን ለማቃለልና ፈጣን አገልግሎት በቅርበት ለህዝቡ ተደራሽ ለማድረግ፣ በክልሉ ሰላምና ፀጥታ ከማስፈን አኳያ የተሻለ ስራ የተከናወነ ቢሆንም አሁንም ወጥነት ባለው መልኩ ከመፈፀም አንፃር ክፍተቶች አሉ ብለዋል።

መድረኩ የተቀሩትን የመንግሥትና የፓርቲ ስራዎችን በሙሉ ለመፈጸም፤ የታዩ ክፍተቶች ላይ በጥልቀት በመወያየት አቅጣጫ ከማስቀመጥ ባለፈ ለመጪው ዓመት የዕቅድ ዝግጅት የሚደረግበት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም