የምገባ ማዕከላት በየቀኑ ምግብ እንድናገኝ በማድረግ እፎይታን የሚሰጡ ናቸው-አቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎች - ኢዜአ አማርኛ
የምገባ ማዕከላት በየቀኑ ምግብ እንድናገኝ በማድረግ እፎይታን የሚሰጡ ናቸው-አቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎች
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 12/2017 (ኢዜአ) :- የምገባ ማዕከላት በየቀኑ ምግብ እንድናገኝ በማድረግ እፎይታን የሚሰጡ ናቸው ሲሉ የተለያዩ አቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።
ኢትዮጵያውያን ስንተባበርና ለአንድ ዓላማ በጋራ ቆመን ስንሰራ የህዝባችንን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደምንችል የምገባ ማዕከላት ማሳያ ናቸው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ 25ኛውንና 26ኛውን የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላትን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት መሠረት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች 26 የምገባ ማዕከላት ተገንብተው በቀን አንድ ጊዜ ምግብ ማግኘት የማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲመገቡ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በቦሌ ክፍለከተማ የሚገኘውና ዛሬ የተመረቀው 26ኛው የምገባ ማዕከል እውን እንዲሆን ሙሉ ወጪውን በመሸፈን በቀጣይም ይህን በጎ ስራ ለማስቀጠል ቃል ለገባው የጉምሩክ ኮሚሽን ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ባለፉት ዓመታት ባለሀብቶችን እና ህብረተሰቡን በማስተባበር በርካታ ሰው ተኮር ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያውያን ስንተባበርና ለአንድ ዓላማ በጋራ ቆመን ስንሰራ የህዝባችንን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ የሚገታን ምንም ነገር የለም ሲሉም ነው ከንቲባዋ የተናገሩት።
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው፥ ከተማ አስተዳደሩ ማህበራዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ለሚያከናውናቸው ሰው ተኮር ተግባራት ኮሚሽኑ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዓለምፀሐይ ሽፈራው፥ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ እና አረጋውያን የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የምገባ ማዕከላት እየተስፋፉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዛሬ የተመረቀው ማዕከልም በቀን አንድ ጊዜ ምግብ ማግኘት የማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመመገብ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፥ ክፍለ ከተማው ሰው ተኮር ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በማዕከሉ ምርቃት በተካሄደው የማዕድ ማጋራት የተሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች በበኩላቸው የምገባ ማዕከሉ መከፈት የኑሮ ጫና ላለብን የህብረተሰብ ክፍሎች እፎይታን የሚሰጥ ነው ብለዋል።
በዛሬው እለት የትንሣኤ በዓልን በደስታ እንዲያሳልፉ የማዕድ ማጋራት መርሀ ግብር በመደረጉም መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በ26ኛው የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከል የአዲስ አበባ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ እንዲሁም የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ፅህፈት ቤት የትንሣኤን በዓል ምክንያት በማድረግ ለአቅመ ደካሞች ማዕድ አጋርተዋል።