በባህር ዳር እና በጎንደር ከተሞች ለ400 አቅመ ደካማ ወገኖች የበዓል መዋያ ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በባህር ዳር እና በጎንደር ከተሞች ለ400 አቅመ ደካማ ወገኖች የበዓል መዋያ ድጋፍ ተደረገ
ባህር ዳር ፣ጎንደር፤ ሚያዚያ 11/2017(ኢዜአ)፡-በባህር ዳር እና በጎንደር ከተሞች የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ400 አቅመ ደካማ ወገኖች የበዓል መዋያ ድጋፍ ተደረገ።
በባህር ዳር ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ያደረገው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባህር ዳር ዲስትሪክት ነው።
በድጋፉ ላይ የተገኙት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው በድጋፍ ስነ ስርአቱ ላይ እንደገለጹት፣ ባንኩ ያደረገው የበዓል መዋያ ድጋፍ አቅመ ደካሞች በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ የሚያስችላቸው ነው።
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተጨማሪ የተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ማህበራትና ግለሰቦች በከተማው ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
እርስ በርስ የመረዳዳትና የመተሳሰብ ባህላችንን በበዓል ወቅት ብቻ ሳይሆን ሁሌም ሊናጠናከር ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባህር ዳር ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ደሞዝ ባልቢ እንደገለፁት ባንኩ ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው 100 የህብረተሰብ ክፍሎች የበዓል መዋያ ድጋፍ አድርጓል።
በዚህም በነፍስ ወከፍ 10 ኪሎ ዱቄት፣ 3 ሊትር ዘይትና ለዶሮና እንቁላል መግዣ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።
በድጋፉ ተጠቃሚ ከሆኑት የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ በቃሉ ጋሹና እማሆይ ፀጋነሽ ይርዳው ድጋፉ የትንሳኤን በዓል ሳይቸገሩ ለማሳለፍ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜና የጎንደር ከተማ የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ 300 አቅም የሌላቸው ወገኖች ዶሮ፣ ዘይትና ሽንኩርት በመለገስ ማዕድ አጋርቷል።
የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው በድገፉ ላይ እንዳሉት በዓሉን በአብሮነት ለማክበር ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
"መረዳዳትና መደጋገፍ የማህበረሰባዊና ሃማኖታዊ እሴቶቻችን መገለጫ ናቸው" ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በዓሉ የሰላምና የደስታ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብሩ እንዲሳካ በገንዘብና በአይነት ድጋፍ ላበረከቱ ለከተማው ባለሀብቶች ምስጋና አቅርበው ህዝቡ ለዘላቂ ሰላም አጥብቆ እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡
በጎንደር ከተማ ድጋፋ ከተደረገላቸው ነዋሪዎች መካከልም እማሆይ መሠረት ችሎት እና አቶ ባይለየኝ መኳንንት መንግስትና ባለሀብቱ ላደረጉላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።