ኢትዮጵያ ከጣልያን ጋር በቱሪዝም ዘርፍ ያላትን ትብብር ለማጠናከር ትሻለች - አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከጣልያን ጋር በቱሪዝም ዘርፍ ያላትን ትብብር ለማጠናከር ትሻለች - አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 11/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ከጣልያን ጋር በቱሪዝም ዘርፍ ያላትን ትብብር የበለጠ የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት በጣልያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ ገለጹ።
አምባሳደር ደሚቱ ከጣልያን የቱሪዝም ሚኒስቴር አማካሪ ሲሞኒ ላንዲኒ እና የካላብሪያ ክልል ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ፊሊፖ ማንኩሶ(ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል።
አምባሳደሯ በውይይቱ በኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ የተሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ከጣልያን ጋር ያለውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላትም ገልጸዋል።
በሁለቱ ሀገራት የቱሪዝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች መካከል የትብብር ስምምነት ለመፈራረም የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል።
በሌላ በኩል አምባሳደር ደሚቱ ከካላብሪያ ክልል ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ጋር ባደረጉት ውይይት የክልሉ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።