የስቅለት በዓል ፍቅርን፣ ይቅር ባይነትንና ትህትናን የምንማርበት ነው- ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
የስቅለት በዓል ፍቅርን፣ ይቅር ባይነትንና ትህትናን የምንማርበት ነው- ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 10/2017(ኢዜአ)፦የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት በዓል አስተምሮ ፍቅር፣ ይቅር ባይነትና ትህትናን በተግባር የገለጠ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች ገለፁ።
የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ ተከብሯል።
የስቅለት በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በተገኙበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በስግደት፣ በጾምና በጸሎት ተከብሯል።
ኢዜአ የበዓሉን አከባበር በማስመልከት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በመገኘት የእምነቱን አባቶች አነጋግሯል።
በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መምህር ዳንኤል ይርጋ ቤተክርስቲያኗ ዕለቱን በስግደት፣ በጾምና ፀሎት ስነ- ስርዓት የምታስበው ክርስቶስ ለሰው ልጆች ነፃ መውጣት የከፈለውን ዋጋ በማሰብ ነው ብለዋል።
የክርስቶስ በመስቀል ፍቅርን፣ አንድነትና ይቅር ባይነት የተገለጠበት የድህነት ቀን መሆኑን አመልክተው፤ ከክርስቶስ ፍቅርን እና ፍጹም ይቅር ባይነትን የምንማርበት እንደሆነ ተናግረዋል።
በዚህም መፋቀርን፣ መተሳሰብና የአብሮነትን ተምሳሌት ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል።
በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የስነ መለኮት ትምህርት ተማሪ መላከ ሰማያት ገትዬ ቃኘው በበኩላቸው፤ የክርስቶስ ስቅለት እኛ የሰው ልጆች እርስ በእርስ እንድንዋደድ የተከፈለ ዋጋ ነው ብለዋል።
ይህን በመገንዘብ እርስ በእርሳችን በመዋደድ ትዕዛዙን መፈፀም አለብን ብለዋል።
ስቅለት ተበድሎ ይቅርታ መባባል እንዳለ ከክርስቶስ የተማርንበት ነው ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመገናኛ ብዙሃን አዘጋጅ መጋቢ ምስጢር ሰሀሉ አድማሱ ናቸው።