በሐረር ከተማ የስቅለት በዓል በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በስግደትና በጸሎት ተከብሯል - ኢዜአ አማርኛ
በሐረር ከተማ የስቅለት በዓል በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በስግደትና በጸሎት ተከብሯል
ሐረር፤ ሚያዚያ 10/2017(ኢዜአ)፦ በሐረር ከተማ የስቅለት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ብሎ የከፈለውን መስዋዕትነት በማሰብ በስግደትና በጸሎት ተከብሯል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በዕለተ ዓርብ የሚከበረውን የስቅለት በዓል በስግደት፣ በጾምና በጸሎት እያከበሩት ነው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሐረር ደብረ ገነት መድሃኒያለም ቤተ ክርስትያን አስተዳዳሪ ሊቀ ጉባዔ አባ ወልደማርያም ተመስገን እንዳሉት እለቱ የክርስቶስ ስቅለት የሚታሰብበትና ክርስቶስ ለሰው ልጆች ብሎ መከራን የተቀበለበት ነው።
ፈጣሪ የሰውን ልጅ ያለ ዋጋ የወደደበት፣ መከራን የተቀበለበትና የፍቅር ጥግ ያሳየበት እለት ነው ያሉት ሊቀ ጉባዔ አባ ወልደማርያም፤ በበዓሉ እሴት መሰረት በአብሮነትና በይቅር ባይነት በዓሉ በጋራ እየተከበረ መሆኑን ተናግረዋል።
ህዝበ ክርስቲያኑ የትንሳኤን በዓል ሲያከብርም ለችግር የተዳረጉና ረዳት የሌላቸውን ሰዎች በማሰብና በመደገፍ በአብሮነት መሆን እንዳለበትም መክረዋል።
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሐረር ሐገረ ስብከት የማርያም ቅዱስ ስም ካቴድራል ቁምስና ቆሞስ አባ ተክለብርሃን የማታዬ እንደገለጹት ኢየሱስ ክርስቶስ በእለተ ዓርብ የደረሰበት ስቃይና ያሳለፈው የመከራ ጊዜ ለፍጹም ፍቅር ሲል እንደሆነ ገልጸዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያሳየውን ፍጹም ፍቅር ምዕመናንም እርስ በርሳቸው ፍቅርና መልካምነትን በማሳየት በዓሉን በአብሮነት እያከበሩት መሆኑን ጠቁመው፤ ምዕመናን የትንሳኤ በዓልን ሲያከብሩ አቅመ ደካሞችና ወላጅ አልባ ህጻናትን በመደገፍ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
የስቅለት በዓልን በስግደት ከፈጣሪ ምህረትንና ይቅርታን በመለመን እያከበሩት መሆኑን የተናገረችው ደግሞ የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይ የሆነችው ምህረት ሙሉጌታ ናት።
አያይዛም የስቅለት በዓልን ክርስቶስ ሲያደርገው የነበረው እርስ በርስ መዋደድንና ፍቅርን ለሰው ልጆች በተግባር በማሳየት እንደሆነም አክላለች።
ዕለተ ዓርብ ክርስቶስ የሰው ልጅን ለማዳን ሲል መከራ የተቀበለበትና የፍቅር ጥግ የታየበት እለት ነው ያለው ደግሞ ዲያቆን አቤል ተሾመ ነው።
እለቱን ክርስቶስ ለሰው ልጆች የከፈለውን መከራና ስቃይ በማሰብ ፍቅር፣ ሰላምና አንድነትን የምናጎለብትበት ነው ሲልም ገልፆታል።