ቀጥታ፡

የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት በዓል ቸርነት እና ፍቅርን ዘወትር እናደርግ ዘንድ የሚያስታውሰን ነው -ቄስ ዮናስ ይገዙ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 10/2017(ኢዜአ)፦የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት በዓል ቸርነት እና ፍቅርን ዘወትር እናደርግ ዘንድ የሚያስታውሰን ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ እየሱስ ፕሬዚዳንት ቄስ ዮናስ ይገዙ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ እየሱስ አማኞች  የስቅለት በዓልን በተለያዩ ሀይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶች አክብረዋል።


 

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ እየሱስ ፕሬዚዳንት ቄስ ዮናስ ይገዙ (ዶ/ር) እንደገለጹት፥ በዓሉ እግዚአብሄር ለሰው ልጆች ፍቅርን እና መስዋእትነትን ያሳየበት ነው።

በመሆኑም የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ የይቅር ባይነትን መንፈስ በመላበስ በአብሮነት መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በዓሉ ቸርነትን እርስ በእርስ እናደርግ ዘንድ የሚያስታውሰን መሆኑን ገልጸዋል።

ቸርነትን የምናደርገው በዓልን ጠብቀን ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ በችግር ላሉ ኑሮ ለጎደለባቸው ህይወት ለከበደባቸው ዘውትር እያደረግን መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል።

የእምነቱ ተከታይ ወይዘሪት ሌንሳ ተክሉ እንደተናገረችው የስቅለት በዓል ክርስቶስ ለሰው ልጆች ፍጹም ፍቅርን ያሳየበት ነው።

በዓሉን በቤተ ክርስቲያን ፈጣሪውን በማመስገን እንዲሁም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በፍቅር ማክበሩን የገለጸው ደግሞ አቶ ዮናስ በላይነህ ነው።

በዓሉ የፍቅር መገለጫ መሆኑን እና ሁሉም እርስ በእርሱ እንዲዋደድ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም