ከኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት የምንማረው ይቅርታ ማድረግን፣ትህትናን እና መከባበርን ነው-ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል - ኢዜአ አማርኛ
ከኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት የምንማረው ይቅርታ ማድረግን፣ትህትናን እና መከባበርን ነው-ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 10/2017(ኢዜአ)፦ከኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት የምንማረው የሰው ልጆች እርስ በርሳቸው ይቅርታ ማድረግን፣ትህትናን እና መከባበርን ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል ገለጹ።
የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት በዓል በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች በስግደት፣ በፆምና በጸሎት እየተከበረ ነው።
በልደታ ማርያም ካቶሊክ ካቴድራል ቤተክርስቲያን እየተከናወነ ባለው የበዓሉ አከባበር የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል፣ ካህናትና ምዕመናን ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፥ ከስቅለት በዓል የምንማረው የሰው ልጆች እርስበርሳቸው ይቅርታ ማድረግን፣ ትህትናን እና መከባበርን ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳንና ሃጥያታቸውን ለማንጻት መስቀል ተሸክሞ መሰቃየቱን፣ መገረፉን፣ በችንካር መቸንከሩንና መሰቀሉን አውስተዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ በሕማማተ መስቀል ፍጹም ፍቅርንና ይቅርታን ማስተማሩን ጠቅሰው፥ የሰው ልጆች ይቅር መባባል፣ እርስ በእርሳቸው መዋደድ እና መከባበር እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ፈጣሪ እኛን ይቅር ብሎናል ያሉት ብጹዕ ካርዲናሉ፥ እኛም የበደሉንን ይቅር በማለት በፍቅርና በአብሮነት መኖርን ማጠናከር አለብን ብለዋል።
ለሀገር እድገትና ሰላም በጋራ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው፥ መጪውን የትንሳኤ በዓልንም አቅም የሌላቸውን ወገኖች በመደገፍ ማክበር እንደሚገባ አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የእምነቱ ተከታዮች በበኩላቸው፥ ፈጣሪ ለእኛ መስዋዕትነት ተቀብሎ እኛን አድኖናል፤ እኛም የበደሉንን ይቅርታ ማድረግና ፍቅርን ማጎልበት አለብን ብለዋል።
መጪውን የትንሳኤ በዓል ባለን አቅም በመረዳዳት እና በማካፈል ማሳለፍ አለብን ያሉት አቶ ታሪኩ ዝናሮ፥ በሰላም፣ በፍቅርና አንድነት በመተሳሰብ ማክበር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በዓሉን በመተሳሰብና በመደጋገፍ በደስታ ማሳለፍ ይገባል ነው ያሉት።
ዶክተር አየለ ዘውዴ በበኩላቸው፥ በሃይማኖቱ አስተምህሮ መሰረት ትህትናን እና ትዕግስትን መሰረት በማድረግ የመቻቻልና የአንድነት እሴትን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።