በአክሱም በእጅ የሚሰሩ የእደ ጥበብ ውጤቶች ከገቢ ምንጭነታቸው ባለፈ መስህቦች ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአክሱም በእጅ የሚሰሩ የእደ ጥበብ ውጤቶች ከገቢ ምንጭነታቸው ባለፈ መስህቦች ሆነዋል

አክሱም፤ ሚያዚያ 10/2017 (ኢዜአ) ፡- በአክሱም በእጅ የሚሰሩ የእደ ጥበብ ውጤቶች ከገቢ ምንጭነታቸው ባለፈ መስህቦች መሆናቸው ተገለጸ።
በአክሱም ከተማ እና አከባቢው አለላን፣ አክርማንና ክርን በማሰናሰል (መግመድ) ማራኪ የሆኑ የእደ ጥበብ ውጤቶች በብዛትና በጥራት ይመረታሉ።
እነዚህን የእደ ጥበብ ውጤቶች በመስራት በብዛት የሚታወቁት ሴቶችና በተለይም እናቶች ሲሆኑ የገቢ ምንጭ በማድረግ ይተዳደሩበታል።
የእደ ጥበብ ውጤቶቹ ለቤት ማስዋቢያና ለመገልገያ የሚያገለግሉ በመሆናቸው ለእነዚሁ ዓላማዎች የሚሸምቷቸው በርካቶች ናቸው።
በዚህም መሰረት የእደ ጥበብ ውጤቶቹ (የአክሱም ጌጦች) ለሰዎች የገቢ ምንጭና ቀልብን የሚገዙ መስህቦች እየሆኑ መምጣታቸው ይነገራል።
ከአክሱም ከተማ ራቅ ባለ የገጠር ቀበሌ የሚኖሩት ወይዘሮ ፀኃይ ትኩእ፣ እነዚህን የጥበብ ውጤቶች ሰትረው ሸጠው ገቢ በማግኘት ቤተሰባቸውን ማስተዳደር ከጀመሩ ውለው አድረዋል።
የመስራት ጥበቡን ከወላጆቻቸው በማየት መልመዳቸውን የሚያስታውሱት ወይዘሮ ፀኃይ፤ አሁን ላይ አሰራሩ ይበልጥ እየተዋበና ማራኪ እየሆነ በገበያም ተፈላጊነቱ መጨመሩን ይናገራሉ።
በዚህም ከራሳቸው አልፈው አምስት ልጆቻቸውን በማስተማር አጠቃላይ ቤተሰብ እያስተዳደሩበት መሆኑን ገልጸው ሙያውን ልጆቻቸውም እንዲለምዱት እገዛ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ከጥበብ ውጤቶቹ ሽጠው በሚያገኙት ገቢ የፍየል እርባታ መጀመራቸውንም ገልጸዋል።
ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ሳራ አሸናፊ፤ በተመሳሳይ የጥበብ ስራዎቹን ሰርተው በመሸጥ ኑሯቸውን እየመሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የእደጥበብ ስራ ፍቅርና ትእግስት የሚጠይቅ የተከበረ ሙያ መሆኑን አንስተው በዚሁ አግባብ እየሰሩ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በአክሱም ከተማ የሚኖረው ወጣት መሓመድ አብዱሰላም፤ የጥበብ ውጤቶቹን ሸምቶ ለውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች በመሸጥ ጥሩ ገቢ እያገኘ መሆኑን ገልፇል።
አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ሌሎች ከተሞችም በመላክ በዚሁ የንግድ ስራ እየተዳደረ ስለመሆኑም አንስቷል።
የአክሱም ከተማ የባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት የእደ-ጥበብ እና ባህል ባለሙያ አብርሀት ግደይ፤ የእደ ጥበብ ውጤቶቹ ከገቢ ማስገኛነትም ባለፈ የቱሪስቶችን ቀልብ እየገዙ መሆኑን ተናግረዋል።
በአክሱምና አከባቢው እነዚህን የጥበብ ውጤቶች የሚሰሩ ከሶስት ሺህ በላይ እናቶች መኖራቸውን ጠቁመው ስራው እየተስፋፋና ገበያውም እየተለመደ መምጣቱን ገልጸዋል።
የእደ ጥበብ ስራው ከገቢ ምንጭነትም ባለፈ የአካባቢውን ሀገር በቀል እውቀቶችና ትውፊትን የሚያስተዋውቅ በመሆኑ ቀጣይነት እንዲኖረው ከተማ አስተዳደሩ እገዛና ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።