የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከሀገር ሰላምና ደህንነት ተልዕኮው ባሻገር ሰብአዊ ተግባራትን አጠናክሮ ይቀጥላል - ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከሀገር ሰላምና ደህንነት ተልዕኮው ባሻገር ሰብአዊ ተግባራትን አጠናክሮ ይቀጥላል - ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 10/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የሀገርና የህዝብን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ ባሻገር በሰብዓዊ ተግባራት ላይ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ መጨውን የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ በመዲናዋ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ አጋርቷል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ፥ ፖሊስ በመላ ሀገሪቱ ሰላምና ደህንነትን የማስጠበቅ ተልዕኮውን ሌት ተቀን በጀግንነት እየተወጣ ነው ብለዋል።
የፌዴራል ፖሊስ አባላት እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ ዋጋ እየከፈሉ ወንጀልን በመከላከል ህዝብን እያገለገሉ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ተቋሙ ህዝባዊነትን በመላበስ የሀገርንና የህዝብን ደህንነት ለማስጠበቅ በየአካባቢው ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የጸጥታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ በሚሰሩ የልማት ስራዎች፣ በማህበራዊና ሰብዓዊ ተግባራት ላይ ፖሊስ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ትልቅ ነው ብለዋል።
ዛሬ የፌዴራል ፖሊስ አመራሮችና አባላት የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በአራዳ ክፍለ ከተማ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ ማጋራታቸውን ጠቅሰው፥ ይህም የኢትዮጵያውያን የመደጋገፍና የአብሮነት እሴትን የሚያጎለብት መሆኑን ተናግረዋል።
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ አያይዘውም አዲስ አበባ በርካታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁነቶች በስፋት የሚስተናገዱባት እና የዓለምን ቀልብ እየሳበች የምትገኝ ከተማ መሆኗን ተናግረዋል።
ፌዴራል ፖሊስ በመዲናዋ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች፣ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ትላልቅ ሁነቶች ያለምንም ችግር እንዲከናወኑ የሚያደርገውን የሁልጊዜም ሚናውን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በማዕድ ማጋራት መርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌታሁን አበራ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የፌዴራል ፖሊስ የኢትዮጵያን ሰላም በማጽናት በሚያደርገው ጉልህ ሚናው ኩራት ይሰማናል ብለዋል።
ተቋሙ የተጣለበትን ሀገራዊ ተልእኮ ከመወጣት ባለፈ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩና ለአቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎች ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያዊ አብሮነትንና መተሳሰብን የሚያሳይ እና የሚያጎለብት እንደሆነም ተናግረዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው ነዋሪዎች መካከል አቶ ሰለሞን ከበደ እና ወይዘሮ ወሰኔ ገዛው፥ የሀገርን ሰላም በሚያስጠበቀው ፌዴራል ፖሊስ የተደረገላቸው ድጋፍ ልዩ የደስታ ስሜት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።
የተደረገላቸው ድጋፍ የትንሳኤን በዓል በደስታ እንዲያሳልፉ የሚያደርጋቸው በመሆኑም አመስግነዋል።