ባንኩ በደብረማርቆስ፣ ወልዲያ፣ ደብረ ብርሃንና ሮቤ ከተሞች ለአቅመ ደካማ ወገኖች የበዓል መዋያ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ባንኩ በደብረማርቆስ፣ ወልዲያ፣ ደብረ ብርሃንና ሮቤ ከተሞች ለአቅመ ደካማ ወገኖች የበዓል መዋያ ድጋፍ አደረገ
ደብረ ማርቆስ/ወልዲያ/ደብረ ብርሃን/ሮቤ፤ ሚያዚያ 10/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በደብረማርቆስ፣ ወልዲያ፣ ደብረ ብርሃንና ሮቤ ከተሞች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች ለትንሳኤ በዓል መዋያ ድጋፍ አድርጓል።
አቅም ለሌላቸው ወገኖች ዛሬ የምግብና የገንዝብ ድጋፍ ያደረጉት በባንኩ የደብረማርቆስ፣ የወልዲያና ደብረ ብርሃን ዲስትሪክቶች ናቸው።
የደብረ ማርቆስ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ አፈወርቅ ሰንደቁ በድጋፍ ሥነ ስርአቱ ላይ እንደገለጹት ባንኩ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ድጋፍ ያደረገው በከተማዋ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ 100 የህብረተሰብ ክፍሎች ነው።
በዚህም ለእያንዳንዳቸው 10 ኪሎ ግራም የዳቦ ዱቄት፣ ሦስት ሊትር ዘይትና ለዶሮ እና ለእንቁላል መግዣ የሚውል 1 ሺህ 500 ብር ድጋፍ ማድርጉን ተናግረዋል።
ባንኩ ከመደበኛ አገልገሎቱ በተጨማሪ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት በማሰብ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመው፣ በቀጣይም ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት የጀመራቸውን ሥራዎች ያጠናክራል ብለዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ስለሺ ተመስገን በበኩላቸው ባንኩ የተቸገሩ ወገኖችን ማሰቡ የሚበረታታና መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወልዲያ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ሰኢድ አሊ ለ100 አቅመ ደካማ ወገኖች ለበዓል መዋያ የሚሆን የምግብና ገንዘብ ድጋፍ መድረጉን ገልጸዋል።
ዲስትሪክቱ በዛሬው እለት በ360ሺህ ብር ወጪ የዳቦ ዱቄት፣ የዘይትና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት የጀመረውን ተግባር በቀጣይም ያጠናክራል ብለዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከልም የከተማው ነዋሪ አቶ ጌታሁን ኪዳነ በሰጡት አስተያየት ዛሬ ባንኩ ያደረገልኝ ድጋፍ ለበዓሉ የሰው እጅ እንዳላይ የሚያደርግ በመሆኑ አመሰግናለሁ ብለዋል።
ድጋፉ አቅም የሌለንን ከስጋት በመታደግ የፋሲካን በዓል ተደስተን አንድናሳልፍ የሚያደርግ ነው ያሉት ደግሞ ሌላዋ የድጋፉ ተጠቃሚ ወይዘሮ ዓለም ሞላ ናቸው።
በተመሳሳይ በባንኩ የደብረ ብርሃን ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ሮቤል ጨበር እንዳሉት ባንኩ በስድስት ቅርንጫፎቹ ለ700 አቅመ ደካሞች የዱቄት፣ የዘይትና ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።
በደብረ ብርሃን ከተማ ዛሬ በተካሄደው የድጋፍ ሥነ ስርአት የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተክለየስ በለጠ እና የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ወርቅአለማሁ ኮስትሬ ተገኝተዋል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሮቤ ዲስትሪክት የፋሲካ በዓልን በማስመልከት በባሌ ሮቤ ከተማ ለ100 አቅመ ደካማና አካል ጉዳተኛ ወገኖች ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፉ ከምግብ እህልና ዘይት በተጨማሪ በነፍስ ወከፍ 1ሺህ 500 ብር በጥሬ ገንዘብ መሆኑን በርክክቡ ወቅት ተመልክቷል።
የዲስትሪክቱ ኃላፊ አቶ ሙዲን ገመዳ በወቅቱ እንደገለጹት፣ ባንኩ ቀደም ሲልም ማህበራዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ ቆይቷል።
የፋሲካ በዓልን በማስመልከት ያደረገው ድጋፍ በከተማው የሚኖሩ አቅመ ደካማና አካል ጉዳተኛ ወገኖች በዓሉን ተደስተው እንዲውሉ በማሰብ እንደሆነ ተናግረዋል።
የሮቤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ጀማነሽ ደሜ በበኩላቸው፤ ባንኩ ለማህበረሰቡ ከሚሰጠው የፋይናንስ አገልግሎት በተጓዳኝ ለአቅመ ደካማና አካል ጉዳተኞች ያደረገው ድጋፍ ለሌሎችም ተቋማት ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖችም ለባንኩ ምስጋና አቅርበዋል።