የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ አጋራ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ አጋራ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ መጪውን የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ በመዲናዋ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ አጋራ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ፥ ፌዴራል ፖሊስ የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ቀን ከሌት ከመስራት ባለፈ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ በሚሰሩ የልማት ስራዎች ላይ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
ፖሊስ የሀገርን ሰላምና ደህንነት ከማረጋገጥ ባለፈ የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ተግባራት ላይ እየተሳተፈ መሆኑንም ገልፀዋል።
በዛሬው እለትም የፌዴራል ፖሊስ አመራሮችና አባላት የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ በአራዳ ክፍለ ከተማ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ ማጋራታቸውን ጠቅሰው ይህም የኢትዮጵያን የመደጋገፍና የአብሮነት እሴት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌታሁን አበራ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩና ለአቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎች ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብሩ ኢትዮጵያዊ አብሮነትንና መተሳሰብን የሚያሳይ እና የሚያጎለብት እንደሆነም ተናግረዋል።