ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንን ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንን ጎበኙ
አዲስ አበባ ፤ሚያዝያ 9/2017(ኢዜአ)፡- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የስራ እንቅስቃሴን ዛሬ ጎብኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ኮሚሽኑ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ምህዳር በእጅጉ ያሻሻሉ የሪፎርም ተግባራትን ማከናወኑን አይተናል ሲሉ አስፍረዋል።
ተቋሙ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ እና ዘመናዊ የዲጂታል አሰራሮችን የተከተለ የደንበኞች አገልግሎት አሰራርን ተግባራዊ አድርጎ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለዘርፉ ትልቅ ዕድል የከፈተ ሲሆን በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ የተገኘው ስኬትም ይህንኑ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በቀጣይ ኮሚሽኑ የጀመረውን አበረታች እና ከኢኮኖሚ ዕቅዶቻችን ጋር የተጣጣመ ዒላማ ተኮር የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስተዋወቅ የኢንቨስትመንት ፍሰትን ማሳደግ ላይ በትኩረት እንዲሰራ አቅጣጫ አስቀምጠናል ሲሉም ገልጸዋል።