ፀሎተ ሐሙስ የሰው ልጆች ትህትናንና እርስ በእርስ መከባበርን የምንማርበት ነው - ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል - ኢዜአ አማርኛ
ፀሎተ ሐሙስ የሰው ልጆች ትህትናንና እርስ በእርስ መከባበርን የምንማርበት ነው - ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2017(ኢዜአ)፦ ፀሎተ ሐሙስ የሰው ልጆች ትህትናን እና እርስ በእርስ መከባበርን የምንማርበት ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል ገለጹ፡፡
የፀሎተ ሐሙስ(ህጽበተ-እግር) ሥነ-ሥርዓት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያ ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል በተገኙበት በልደታ ማርያም ካቶሊክ ካቴድራል ተከናውኗል፡፡
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያ ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ ፀሎተ ሐሙስ ኢየሱስ ክርስቶስ ትህትናን ያስተመረበት ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ዝቅ አድርጎ የደቀ መዛሙራቱን እግር ማጠቡን አስታውሰው፤ ይህም የሰው ልጆች እርስ በእርሳችን እንድንከባበርና እንድንዋደድ የሚያስተምር ነው ብለዋል።
ይህንን የትህትና እና የመተዛዘን ሃይማኖታዊ እሴት የሰው ልጆች ሁሉ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው አካል ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የሃይማኖት አባቶችም ይህንን የሃይማኖት እሴት ለምዕመናን ማስረጽ እና ለሀገራችን እድገትና ሰላም መስራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡
መጪው የትንሳዔ በዓል እንደመሆኑ መጠን በጾም ወቅት የነበረው የመረዳዳት እሴት በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጥል እንዳለበት አመላክተዋል፡፡
ሕዝበ ክርስቲያኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን ትህትና እርስ በእርስ መከባበርን በአርያነት መውሰድ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።