ቀጥታ፡

ህዝበ ክርስትያኑ ኢየሱስ ክርስቶስ በፀሎተ ሀሙስ ካሳየው ፍፁም ትህትና በመማር እርስ በርስ በፍቅርና በመተሳሰብ ሊኖሩ ይገባል - የሃይማኖት አባትና ምዕመናን

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2017(ኢዜአ)፦ ህዝበ ክርስትያኑ ኢየሱስ ክርስቶስ በፀሎተ ሀሙስ የሐዋርያትን እግር በማጠብ ካሳየው ፍፁም ትህትና በመማር እርስ በርስ በፍቅርና በመተሳሰብ ሊኖሩ እንደሚገባ የሃይማኖት አባትና ምዕመናን ገለፁ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከትንሳዔ በፊት ያለውን ሳምንት ሰሞነ ሕማማት በማለት ይዘከራል።

በሕማማት ሳምንት ከሚታሰቡት ዕለቶች መካከል የዛሬዋ ቀን ፀሎተ ሐሙስ ወይም ህፅበተ እግር አንዱ ነው።

ስነስርዓቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ የቤተክርስቲያኗ ጳጳሳት፣ ካህናት እና ምዕመናን በተገኙበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተካሂዷል።

ዕለቱን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የጳጳሳቱን እግር በማጠብ የኢየሱስ ክርስቶስ ትህትናና አክብሮት መገለጫ የሆነው የህፅበት እግር ሥነ ስርዓት እንዲሁም በስግደትና ቅዳሴ ተከብሯል።


 

በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የትምህርት ክፍል ኃላፊ ሊቀጠበብት ናትናኤል ገብረማርያም እንዳሉት ህፅበተ እግር ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠብ ፍፁም ትህትናን ያስተማረበት እለት ነው።

ስለሆነም ምዕመናን ከዚህ በመማር በትህትና፣ በፍቅርና በአንድነት መኖርን ሊማሩ ይገባል ብለዋል።


 

ኢዜአ ያነጋገራቸው የእምነቱ ተከታዮች በበኩላቸው ከኢየሱስ ክርስቶስ ትህትናን በመማር እርስ በእርስ መደጋገፍና በአንድነት መኖር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አብነት አለማየሁ እንዳለው በዓሉ ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠብ ትህትናን ያስተማረበት ነው።


 

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ አዜብ ወልደሚካኤል በበኩላቸው ፀሎተ ሀሙስ ትህትናና ለሰዎች መልካም ማድረግን የምንማርበት ነው ብለዋል።


 

ከበዓሉ የተማርነውን ትህትናና ፍቅርን በየእለት ህይወታችን በተግባር መተርጎም ይገባናል ሲል የተናገረው ደግሞ ወጣት ጌትነት ደስታ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም