ቀጥታ፡

በመጪው የትንሳኤ በዓል አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲኖር ዝግጅት ተደርጓል-የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 9/2017(ኢዜአ):- በመጪው የትንሳኤ በዓል አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲኖር ዝግጅት መደረጉን የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ታዬ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤በመጪው የትንሳኤ በዓል የኤሌክትሪክ አገልግሎት በተሻለ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል።

የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ምክንያት 47 በመቶ የዛፎች ቅርንጫፍ መሆኑ በጥናት ተለይቷል ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፥ ባለፉት ሁለት ወራት ለኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ቅርብ የሆኑ ዛፎችን እና ቅርንጫፎችን በማስወገድ የቅድመ መከላከል ሥራ ሲከናወን መቆየቱን አስረድተዋል።

የኃይል መቆራረጥ ቢያጋጥም ፈጣን የጥገና አገልግሎት በመስጠት ወደ አገልግሎት ለመመለስ ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ አገልግሎት የሚሰጥ ቡድን መዋቀሩን ገልጸው፥ቡድኑ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉንም አብራርተዋል።

ከሰው ኃይል ዝግጅት ባለፈ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር ለአገልግሎቱ መሳለጥ የሚያገለግሉ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ግብዓት የማሟላት ሥራ መከናወኑንም አስታውቀዋል።

ኀብረተሰቡ በበዓል ወቅት የሚኖረውን የኃይል ጫና ለመቀነስ ከበዓል በፊት መከናወን የሚችሉ ሥራዎችን አስቀድሞ ቢያከናውን የተሻለ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኀብረተሰቡ ኤሌክትሪክን ከተጠቀመ በኋላ በአግባቡ በማጥፋት እና ሶኬቶችን በመንቀል ራሱን ከአደጋ ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል።

በዓሉን አስመልክቶ ኀብረተሰቡ የሚገለገልበት ቁሳቁስ ኃይል ቆጣቢ እንዲሁም ለአደጋ የማያጋልጥ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚኖርበትም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የቅድመ ክፍያ አገልግሎት ተጠቃሚዎች የኃይል አቅርቦት እንዳይስተጓጎልባቸው አስቀድመው ካርዳቸውን እንዲያስሞሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የካርድ ቆጣሪ የሚጠቀሙ ደንበኞችን ለማስተናገድ አገልግሎቱ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል።

መሰረተ ልማት ላይ የሚፈጸም ስርቆት ለኤሌክትሪክ መቆራረጥ አንዱ ምክንያት መሆኑን የገለጹት አቶ መላኩ፥ ኀብረተሰቡ የስርቆት ወንጀሎችን በማጋለጥ የድርሻውን ሚና ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም