ቀጥታ፡

መጪው የስቅለትና የፋሲካ በዓልን በማስመልከት ለፀጥታ አካላት የስራ መመሪያ ተሰጠ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 9/2017(ኢዜአ):- መጪው የስቅለትና የፋሲካ በዓልን በማስመልከት ለፀጥታ አካላት አመራሮች የበዓል ቅድመ ዝግጅቱን አስመልክቶ የስራ መመሪያ ተሰጥቷል።

በአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ልዩ ልዩ የፀጥታ አካላት በተገኙበት በዓላቱን አስመልክቶ የተዘጋጀ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በመድረኩ በቀጣይ ቀናት ስለሚከናወኑ ስራዎችና የሚደረጉ የፀጥታ አካላትን ስምሪት አስመልክቶ አቅጣጫ መሰጠቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።


 

ከዚህ ቀደም በሃይማኖታዊ እና ህዝባዊ በዓላት ያሉ መልካም ተሞክሮዎችን በመውሰድ ቀጣይ የሚከበሩ የስቅለትና የትንሣኤ በዓላት አከባበር በስኬት እንዲጠናቀቅ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ተመላክቷል።

በበዓል ሰሞን ሊከሰቱ የሚችሉ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ማጭበርበሮች እንዲሁም ሽማቹ በሚጠቀማቸው የምግብ ተዋፅኦዎች ላይ ባዕድ ነገር ቀላቅለው ወደ ገበያ ይዘው የሚወጡ ግለሰቦች ሊኖሩ ስለሚችሉ በግብይት ወቅት ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም መልዕክት ተላልፏል።

በአብያተ ክርስቲያናትና በገበያ ስፍራዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ጠንካራ ህግ የማስከበር ስራ ከመስራት ባሻገር ተገቢነት የሌለውን የዋጋ ጭማሪ ለመቆጣጠር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑም በውይይቱ ተነስቷል።


 

በበዓል ሰሞን ሊከሰቱ የሚችሉ የወንጀልና ትራፊክ አደጋዎችን ለመከላከል በርከት ያለ የፀጥታ ኃይል በማሰማራት ቴክኖሎጂን በመጠቀም በተለይም አልኮል ጠጥተው የሚያሽከረክሩና የተለያዩ የደምብ መተላለፍ ጥፋቶችን ለመከላከል በተጠኑ የከተማዋ አካባቢዎች ተገቢው የቁጥጥርና የፍተሻ ስራ ይሰራል ተብሏል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ጌቱ አርጋው እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።

ህብረተሰቡም ከፀጥታ አካላት ጋር እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲሁም የፀጥታ አካላት አመራሮችና አባላት በጥብቅ ዲሲፕሊን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማሳሰባቸውን አዲስ አበባ ፖሊስ በመረጃው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም