የፀሎተ ሐሙስ ‘ህፅበተ እግር” ሥነ ስርዓት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እየተካሄደ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
የፀሎተ ሐሙስ ‘ህፅበተ እግር” ሥነ ስርዓት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እየተካሄደ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 9/2017(ኢዜአ)፦ የኢየሱስ ክርስቶስ ትህትና እና አክብሮት የተገለፀበት የፀሎተ ሐሙስ ‘ህፅበተ እግር” ሥነ ስርዓት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እየተካሄደ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከትንሳዔ አንድ ሳምንት በፊት ያለውን ሳምንት ሰሙነ ሕማማት (የሕማማት ሳምንት) በማለት ትዘክረዋለች።
በሕማማት ሳምንት ከሚታሰቡት ዕለቶች መካከል የዛሬዋ ቀን ፀሎተ ሐሙስ፣ ህፅበተ-እግር ፣ የምሥጢር ቀን፣ የሀዲስ ኪዳን እና የነፃነት ሐሙስ ተብላ ትጠራለች።
ፀሎተ ሐሙስ ኢየሱስ ክርስቶስ የሐዋርያትን እግር ዝቅ ብሎ በማጠብ ፍፁም ትህትናንና አክብሮትን ያሳየበት በዓል ነው።
ዕለቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ የቤተክርስቲያኗ ጳጳሳት፣ ካህናት እና ምዕመናን በተገኙበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እየተካሄደ ይገኛል።
በቤተ ክርስቲያኗ አስተምህሮ ካህናት አባቶች ከዲያቆናት እስከ ምዕመናን ድረስ ዝቅ ብለው እግር በማጠብ የክርስቶስን ትህትና በተግባር ይሰብካሉ።
በዛሬው ዕለትም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የጳጳሳቱን እግር በማጠብ የኢየሱስ ክርስቶስ ትህትናና አክብሮት መገለጫ የሆነው የ“ህጽበት እግር” ስነ ስርዓት አከናውነዋል።