ቀጥታ፡

በመጪው የትንሳዔ በዓል የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ነው-አገልግሎቱ

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 9/2017 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በመጪው የትንሳዔ በዓል የኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ ችግርን ለመቀነስ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ተቋሙ በበዓሉ ዋዜማና በዕለቱ የኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ ሳይፈጠር ለተጠቃሚው ለማቅረብ፣ ከተከሰተም አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ግብረ-ኃይል በየደረጃው በማዋቀር ወደ ስራ መግባቱን ገልጿል፡፡

ደንበኞች የኃይል መቆራረጥ ችግር እንዳያጋጥም የኃይል ጭነት በማይበዛባቸው ሰዓታት በተለይ ከምሽቱ 4፡00 እስከ ንጋቱ 12፡00 ባሉት ጊዜያት ቢጠቀሙ እንደሚመከር ነው የገለጸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ደንበኞች በቤት ውስጥ የሚገለገሉባቸውን የኤሌክትሪክ ቁሳቁሶች ኃይል ቆጣቢና ለአደጋ የማያጋልጡ እንዲሆኑም አስገንዝቧል፡፡

ለኤሌክትሪክ አደጋ እና ለተለያዩ ጥያቄዎች በ905 እና 904 ነፃ የጥሪ ማዕከል በመደወል ማሳወቅ እንደሚቻል ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም