የአማራ ክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የጎንደር ከተማን የኮሪደር ልማት የምሽት ድባብ ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የጎንደር ከተማን የኮሪደር ልማት የምሽት ድባብ ጎበኙ
ጎንደር፤ ሚያዝያ 8/2017(ኢዜአ)፦ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ የተመራ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ቡድን በጎንደር ከተማ የፒያሳና የመስቀል አደባባይ አካባቢን የኮሪደር ልማት የምሽት ድባብ ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
የስራ ሃላፊዎቹ በአለም ቅርስነት የተመዘገበውን የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት የቅርስ ጥገናና እድሳት ስራም ጎብኝተዋል።
12 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውና ከፒያሳ ኮሌጅ ማዞሪያ፣ ማራኪ፣ አዘዞና አየር ማረፊያ ድረስ የሚዘልቀው 2ኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስራም በምሽት ጭምር ስራው እየተከናወነ መሆኑን ተመልክተዋል፡፡
የኮሪደር ልማት ስራው የአግረኛና የብስክሌት መንገዶችን፣ የጎርፍ መፋሰሻ ቦዮችንና የአረንጓዴ መናፈሻ ግንባታዎችን ጨምሮ የስማርት ፖሎች ተከላና የመጸዳጃ ቤቶች አገልግሎቶችን ያካተተ ሆኖ እየተገነባ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
በምሽት ጉብኝቱ ላይ የርዕሰ መስተዳድሩ የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ አማካሪ ዶክተር መስፍን አበጀን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ፣ የማእከላዊ ጎንደር ዞንና የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ለከፍተኛ የስራ ሃላፊዎቹ ባደረጉት ገለጻ ፕሮጀክቶቹ በፌዴራልና በክልሉ መንግስት ድጋፍና ክትትል እየተገነቡ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በከተማው እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶችም የከተማዋን ገጽታ በመገንባት፣ ቱሪዝምና ኢንቨስትመንት በመሳብ፣ የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን አብራርተዋል።