በአፋር መገናኛ ብዙሃን ድርጅት በተቋም ግንባታ ረገድ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው - የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር መገናኛ ብዙሃን ድርጅት በተቋም ግንባታ ረገድ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው - የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን
ሰመራ፤ ሚያዝያ 8/2017 (ኢዜአ)፡- የአፋር መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ተልዕኮውን ከግብ ለማድረስ እንዲያስችለው እያከናወነ የሚገኘውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ገለፀ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የሱፐርቪዥን ቡድን ለድጋፍና ክትትል ሠመራ ከተማ በመገኘት የክልሉን መገናኛ ብዙሃን ድርጅት የስራ እንቅሰቃሴና እየተሰራ ያለውን ሁለገብ ህንፃ እንዲሁም የሠመራ ማህበረሰብ ሬዲዮን የስራ እንቅሰቃሴ ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የሚዲያና ማስታወቂያ ክትትል መሪ ስራ አሰፈፃሚ እና የሱፐር ቪዥኑ ቡድን መሪ አቶ ዴሬሳ ተረፈ እንደተናገሩት ድርጅቱ በክልሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እየሰራ ነው።
በተለይም የአገሪቷን ብሎም የክልሉን የልማት ስራዎችን ለህዝቡ ተደራሽ ከማድረግ አኳያ እንደ ድልድይ ሁኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ድርጅቱ በተለይም የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት እንዲያስችለው እያካሄደ ያለውን ተቋማዊ እንቅስቃሴ አጠናክሮ ማስቀጠል ላይ ማተኮር አለበት ብለዋል።
የሠመራ ማህበረሰብ ሬዲዮን ማጠናከርና መደገፍ ላይም ከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባው አቶ ዴሬሳ አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የማህበረሰብና የሐይማኖት መገናኛ ብዙሃን ክትትል ዴስክ ሐላፊ አቶ ሁሴን ሻንቆ በበኩላቸው ድርጅቱ ማህበረሰቡን በመረጃ ተደራሽ ከማድረግ አኳያ እያደረገ ያለው እንቅሰቃሴዎች አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል።
አነዚህን ተግባራት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልፀዋል።
የአፋር መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አህመድ ኮሎይታ እንዳሉት " ሚዲያው አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተገኘ ፍሬ ነው"።
ላለፉት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች አፋር የራሱ ሚዲያ ባለቤት እንዳይሆን ተደርጎ መቆየቱን ጠቁመው አሁን ላይ የሚዲያ ባለቤት መሆን ችሏል ብለዋል።
በዚህም መሠረት የክልሉን ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች፣ የህዝቡን ባህልና እሴቱን ተደራሽ ከማድረግ አኳያ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።