የግማሽ ምዕተ ዓመቱ ታሪካዊ ጉብኝት፡- - ኢዜአ አማርኛ
የግማሽ ምዕተ ዓመቱ ታሪካዊ ጉብኝት፡-

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቬይትናም ጉዞ
በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ነሃሴ 2018 የቬይትናም የቀድሞ ፕሬዝዳንት ትራን ዳይ ኳንግ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደረጉ የመጀመሪያው የቬይትናም መሪ ናቸው።
የፕሬዝዳንቱ የሶስት ቀናት ጉብኝት ትኩረት በኢትዮጵያ እና ቬይትናም መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ትብብርን ማጠናከርን ያለመ ነበር።
ኳንግ በወቅቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን አድርገዋል።
ከፕሬዝዳንቱ ጋር ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የቬይትናም የልዑካን ቡድን የቢዝነስ ማህበረሰብ አባላት ከግሉ ዘርፍ የቢዝነስ ማህበረሰብ አባላት ጋር ውይይት ያደረገ ሲሆን ምክክሩ በሀገራቱ የንግድ ተወካዮች መካከል ቋሚ ትስስርን መፍጠር ያለመ ነው።
የአገራቱን ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት መሰረት በማድረግ የሁለትዮሽ እና የባለብዝሃ ወገን ትብብር ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል በወቅቱ።
ኢትዮጵያ እና ቬይትናም በምጣኔ ሀብት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በፓርላማ ለፓርላማ፣ እና በመሳሰሉት የልማት መስኮች በትብብር ለመስራት ከዚህ በፊት የፈረሟቸውን ስምምነቶች ሥራ ላይ ለማዋል እንደሚገባም ተስማምተው ነበር።
ትራን ዳይ ኳንግ ኢትዮጵያን ከጎበኙ ሰባት ዓመታት አለፉ።
ከሰባት ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ እና ቬይትናም የሁለትዮሽ ትብብር ታሪክ ኢትዮጵያዊ መሪ የደቡብ ምስራቅ ኤስያዊቷን ሀገር መሬት ለመጀመሪያ ጊዜ ረገጠ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ቬይትናም ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) ቬይትናምን የጎበኙ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መሪ ናቸው።
ይህ በሁለቱ ሀገራት መካከል የሁለትዮሽ ትብብር ዑደት ውስጥ ትልቅ ትርጉም እና አንድምታ ያለው ነው።
ኢትዮጵያ እና ቬይትናም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1976 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ትብብር እ.አ.አ በ2026 50ኛ ዓመቱን ይደፍናል።
በነዚህ ዓመታት ውስጥ በቬይትናም በመሪ ደረጃ የጎበኘ የኢትዮጵያ መሪ የለም።
ከዚህ አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቬይትናምን መጎብኘታቸው በሁለቱ ሀገራት ትብብር የሚነሱ ታሪካዊ መሪ ያደርጋቸዋል።
ቬይትናም ኒውስ፣ ቮይ ኦፍ ቬይትናም፣ ናን ዳን ኦንላይን እና ቬይትናም ፕላስ የተለያዩ የሀገሪቷ መገናኛ ብዙሃን ታሪካዊው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ትብብር ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው ዘግበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቬይትናም በሚኖራቸው ቆይታ በ2025 የፒ4ጂ ቬይትናም ጉባኤ ላይ እንደተሳተፉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በቆይታቸው ከቬይትናም የፀሃይ ኃይል ማመንጫዎች በማምረት ወደ ውጭ የሚልከውን ቶዮ ሶላር የተባለውን ፋብሪካ ጎብኝተዋል።
ድርጅቱ በቅርቡ በሀዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ በመግባት በኢትዮጵያ ሥራ ጀምሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርጅቱ ከፀሃይ ኃይል ማመንጫ ምርት ባሻገር የኃይል ማመንጫ ፋብሪካ እንዲያቋቁም አበረታተዋል።
ይኽም ሀገራችን ከያዘችው የአረንጓዴ አሻራ ፖሊሲ ጋር የተናበበ በማደግ ላይ ላለው የኃይል ጥያቄም ምላሽ በመስጠት ሊያግዝ የሚችል መሆኑን መግለጻቸውን የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያመለክታል።
የቬይትናም መገናኛ ብዙሃን ጉብኝቱ የሀገራቱን የሁለትዮሽ እና የባለብዝሃ ወገን ትብብር እንደሚያጠናክር በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ እና ቬይትናም ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሁለትዮሽ ትብብራቸውን የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችላቸውን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በየካቲት ወር 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተደረገው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እና ቬይትናም የጋራ የፖለቲካ ምክክር የዚሁ ፍላጎት ማሳያ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታሪካዊ ጉብኝት ለኢትዮጵያ እና ቬይትናም ግንኙነት የላቀ ትብብር እና ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ ከፋች ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው አካል የሆነ ውይይት ከቬይትናም ኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ፀሃፊ ጋር በፓርቲው ማዕከላዊ ጽሕፈት ቤት አካሂደዋል። በውይይታቸውም በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ጉዳዮች ብሎም በሀገራዊ ልማት እና አስተዳደር ጉዳዮች መክረዋል።
የቬይትናም ጠቅላይ ሚኒስትር ፋም ሚን ቺን በቤተ መንግሥታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ይፋዊ የአቀባበል ስነ-ስርዓት አድርገውላቸዋል።
ሁለቱ መሪዎችና የልኡካን ቡድኖቻቸው የሁለትዮሽ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፥ በሁለቱ ሀገራት የተካሄዱ ማሻሻያዎችን እንዲሁም ለትብበር የሚሆኑ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በተለይም የልምድ ልውውጥንና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ ተለዋውጠዋል።
መሪዎቹ የትብብር ሰነዶችን የፊርማ ስነ-ስርዓት ላይም የተገኙ ሲሆን፥ በንግድ እና በትምህርት ትብብር ላይ የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈርመዋል። በተጨማሪም በአዲስ አበባ እና በሃኖይ መካከል በኢትዮጵያ አየር መንገድ የቀጥታ በረራ መንገድ የሚያመቻች የሲቪል አቪዬሽን ስምምነት ተደርጓል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቬይትናም ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከተመሰረተ ከሃምሳ አመታት በኋላ የመንግስት መሪ ያደረጉት የመጀመሪያ ይፋዊ የኦፊሴላዊ ጉብኝት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ2025 የፒ4ጂ ቬይትናም ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት “ዘላቂ እና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ አረንጓዴ ሽግግር” በሚል ጭብጥ እየተካሄደ ባለው የ2025 ፒ4ጂ ቬይትናም ጉባኤ የአየር ንብረት ጥበቃን ለማራመድ አስፈላጊ የሆኑ ሶስት ቁልፍ የተግባር ነጥቦችን አፅንዖት ሰጥቼ አንስቻለሁ ብለዋል።
በዚህም አንደኛ የአየር ንብረት ጥበቃ የገንዘብ አቅርቦትን የቅድሚያ ቅድሚያ በመስጠት በቂ፣ ተገማች እና ዘላቂ በሆኑ ምንጮች ማረጋገጥ ይኖርብናል ሲሉም ገልጸዋል።
ሁለተኛ ዘላቂ ልማትን ለመደገፍ እና የአኅጉሩን ወሳኝ ሥነምኅዳር ጥበቃ ለማድረግ በአለም የኃይል ምንጭ ኢንቬስትመንት ሽፋን ውስጥ የአፍሪካን ድርሻ በአሁኑ ወቅት ካለበት ሁለት ከመቶ በ2030 ወደ ሃያ ከመቶ ማሳደግ ይገባናል ነው ያሉት።
ሶስተኛ የብዝኀ ሕይወት ጥፋትን እና የምድር መራቆትን በመዋጋት ተፈጥሮን ለመጠበቅ አፋጣኝ ርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
ይኽም እንደ አረንጓዴ አሻራ ያሉ ሕዝባዊ ሥራዎችን በገንዘብ መደገፍን በዚህም ለየአካባቢው ኅብረተሰብ ከአድልዎ የፀዳና ፍትኀዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥን ያካትታል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የቬይትናም ጠቅላይ ሚኒስተር ፋም ሚን ቺን በይፋዊ ጉብኝታችን ወቅት ላደረጉት የደመቀ አቀባበል እና የክብር መስተንግዶ አመሰግነዋል።
“ኢትዮጵያና ቬይትናም የሚያመሳስሏቸው ብዙ የጋራ ጉዳዮች አሏቸው። ሁለታችንም ትልቅ እና ለሥራ የተነሳሳ ወጣት ሕዝብ ያለን፣ ለልማት እና እድገት የቆረጥን እንዲሁም በታሪካችን ሂደትም በፅናታችን የምንታወቅ ሀገራት ነን።
ውይይታችን በንቁ ተሳትፎ የሚገለጥ እና ጥልቀትም የነበረው ነበር። ለጋራ እድገት እና ትብብር ያለንን ፅኑ የጋራ ተነሳሽነትም አንፀባርቀናል። የሃሳብ ልውውጣችን በሁለቱ ሀገሮቻችን መካከል ለጠንካራ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር በር ከፍቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ፋም ሚን ቺን በቅርብ ኢትዮጵያን በሚጎበኙበት ወቅት የጋራ ርዕዮቻችንን የበለጠ የምናጠናክርበት እና በዛሬው የአለማችን አውድ የሁለትዮሽ ግንኙነታችንን ይበልጥ የምናፀናበት ይሆናል” ሲሉ አረጋግጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሃኖይ እየተገነባ የሚገኘውን ትልቅ የዘመነ ከተማ (የስማርት ሲቲ) ፕሮጀክት ጎብኝተዋል።
ይኽም ለኢትዮጵያ የከተማ ልማት ሥራ የሚሆን ተሞክሮ የመቅሰም ተግባር አካል መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ጉብኝቱ ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር በመላው ኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ የዘመናዊ ከተማ ፕሮጀክቶችን ለማላቅ የሚደረግ ፍላጎትና ጥረትን እንደሚያሳይ ገልጿል።
ከቬይትናም ፕሬዝዳንት ጄነራል ሉዎንግ ኩዎንግ ጋር ውይይት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ከብሔራዊ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ትራን ታንህ ማን ጋርም መክረዋል።
ውይይቶቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቬይትናም ሶሻሊስት ሪፐብሊክ የሚያደርጉትን ይፋዊ ጉብኝት አካል መሆኑን ነው።
በሁለቱም ውይይቶች ስለ ሀገረ መንግሥት ቀጣይነት፣ የፖለቲካ ትብብር፣ የለውጥ ጥረቶች የተነሱ ሲሆን በብዙ ዘርፎች የሁለትዮሽ ትስስሮችን እና ትብብሮችን ይበልጥ ለማጠናከር የሚቻልባቸው መንገዶች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።