ሰላማዊ ትግልን ማእከል ላደረገ የፖለቲካ አካሄድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናቸውን ማጠናከር አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ሰላማዊ ትግልን ማእከል ላደረገ የፖለቲካ አካሄድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናቸውን ማጠናከር አለባቸው
አዲስ አበባ ሚያዚያ 08/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሰላማዊ ትግልን ማእከል ያደረገ የፖለቲካ አካሄድ እውን እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።
የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ''ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለጠንካራ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ'' በሚል መሪ ሀሳብ 11ኛ ጠቅላላ ጉባዔውን አካሄዷል።
ጉባዔው አዲስ የጋራ ምክር ቤቱን የሚመራ ስራ አስፈጻሚ አባላት የመረጠ ሲሆን በዚሁ መሰረት አቶ ሰለሞን ታፈስ ከአዲስ ትውልድ ፓርቲ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሆነው ተመርጠዋል።
ከብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አቶ ሞገስ ኢደኤ ደግሞ የምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ አቶ ታሪኩ ድንበሩ የምክር ቤቱ ጸሐፊ ሆነው ተመርጠዋል።
በጉባዔው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ፤ በአገሪቷ ሰላምን ማእከል ያደረገ የፖለቲካ ባህል እንዲዳብር የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ስልጣን ለመያዝ ከውይይትና ሰላማዊ ድርድር ይልቅ መሳሪያና ሀይልን መጠቀም የቆየ ልማድ በመሆኑ ችግሩ ዘርፈ ብዙ ጉዳት ሲያስከትል መቆየቱንም ተናግረዋል።
በዚህ ዘመንም በሀሳብና በወይይት የታጀበ ሰላማዊ የፖለቲካ ባህልን እውን በማድረግ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ መገንባት ያስፈልጋልም ብለዋል።
ይህም የመጠፋፋት የፖለቲካ ባህል እንዲገታ በማድረግ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ የፖለቲካ ምህዳር እንዲዘረጋና ዘላቂ ልማት እንዲረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ነመራ ቡሊ በበኩላቸው ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመትከል የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የሰፈነባቸው አገራት ተሞክሮም እንደሚያሳየው ዴሞክራሲ አጠቃላይ እድገት እንዲፋጠን፣ የህዝብ ተሳትፎ እንዲጎለብት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።
በክልሉም ህዝቡን ከድህነት ወደ ብልጽግና ለማሻገር በሚደረገው ርብርብ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ ትግልን በመላበስ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት መትጋት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ሀሳብና ውይይት ባህል የሆነበት የፖለቲካ ባህል እንዲለመድ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጸሐፊ አቶ ታሪኩ ድንበሩ ናቸው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነት ቢኖርም በውይይትና በሀሳብ የበላይነት ማሸነፍ እንደሚቻል ለአባሎቻቸው በማሳወቅ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ አባል የሆነው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ አቶ ኤርሚያስ ተገኝ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ሲያጋጥም የነበረው ችግር የሁሉም መሆኑን በመረዳት አብሮ መቆምና መታገል ይገባል ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀጣይነት ባለው መልኩ በጋራ በመሆን ሰላማዊ ትግልን ማጠናከር እንደሚገባም አስረድተዋል።