በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ ለሶስተ ዓመታት የሚቆይ ሁለተኛ ዙር የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ፕሮግራም ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ ለሶስተ ዓመታት የሚቆይ ሁለተኛ ዙር የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ፕሮግራም ተጀመረ
ገንዳ ውኃ፤ ሚያዚያ 8/2017(ኢዜአ)፦ በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ ለሶስተ ዓመታት የሚካሄድ ሁለተኛው ዙር የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ(ሴፍቲኔት) ፕሮግራም መጀመሩን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ።
በፕሮግራሙም ከ750 በላይ የቤተሰብ መሪዎችን የኑሮ ደረጃ በዘላቂነት ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሰራም የከተማው አስተዳደር አስታውቋል፡፡
በፕሮግራሙ ማስጀመሪያ ላይ የገንዳ ውኃ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ አብዱልከሪም ሙሀመድ እንደገለጹት ሁለተኛው ዙር የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ፕሮግራም ለሶስት ዓመታት የሚዘልቅ ነው፡፡
በፕሮግራሙ ከተቀፉት ውስጥ 1ሺህ 146 የቤተሰብ አባላት ያሏቸው 389 የቤተሰብ መሪዎችን በልማት በማሳተፍ እንዲጠቀሙ የሚደረግ ሲሆን ቀሪዎቹ በቀጥታ ድጋፍ የሚደረግላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።
መስራት የሚችሉ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች በከተማዋ ጽዳትና ውበት እንዲሁም የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ላይ በመሰማራት የከተማዋን ገጽታ ለመቀየር እንደሚሰሩ ተመልክቷል።
በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ ባዘጋጀው 3 ሄክታር መሬት ላይ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና ሌሎች የከተማ ግብርና ስራዎች ላይ በመሰማራት ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።
በከተማው የምግብ ዋስትናና ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ማስተባባሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አንዱዓለም አሰፋ በበኩላቸው፤ ለፕሮግራሙ ማስፈጸሚያ አራት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት እንደተመደበ ተናግረዋል፡፡
ተጠቃሚዎቹ የቁጠባ ባህልን እንዲያዳብሩ በማድረግና በከተማ ግብርና ተሰማርተው አትክልትና ፍራፍሬ እንዲያለሙ ይሰራል ብለዋል።
በፕሮግራሙ ከሚሳተፉት መካከል ወይዘሮ ሰናይት አባይ በሰጡት አስተያየት፤ በፕሮግራሙ ተሳትፈው ኑሯቸውን ለማሻሻል ጥረት እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።
ከዚህ በፊት በፕሮግራሙ በመሳተፍ ባፈሩት ጥሪት ህይወታቸውን እንዳሻሻሉ ጠቁመው ተጨማሪ ስራ ሰርተው በመቆጠብ ለውጥ ለማምጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ሙሉየ ግርማ በበኩላቸው በፕሮግራሙ በመታቀፌ የሶስት ቤተሰቤን ህይወት ለመለወጥና የከተማዬን ገጽታ ለማሻሻል ቆርጬ ተነስቻለሁ ብለዋል፡፡